Mols.gov.et

ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ስድስት ወራት ከ2,300 በላይ ባለሙያዎችን ለሥራ ገበያው በማቅረብ

February 10, 2026
ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ስድስት ወራት ከ2,300 በላይ ባለሙያዎችን ለሥራ ገበያው በማቅረብ የዘርፉን ተወዳዳሪነት እያረጋገጠ ነው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ለኢኮኖሚያችን እምቅ አቅም ያለው ቢሆን፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት እና የሀገር በቀል ምግቦቻችን በዘመናዊው መስተንግዶ ውስጥ በሚፈለገው መጠን አለመካተታቸው በዘርፉ ገቢና ተወዳዳሪነት ላይ የራሱ የሆነ ጫና ሲፈጥር ቆይቷል። ይህንን ክፍተት ለመሙላት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋም የሆነው የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት፣ ተቋማዊ አሰራሩን በ ISO-21001:2018 ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ በማደራጀት ሰፊ የክህሎት ማበልጸጊያ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በዚህም ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ስድስት ወራት በዳቦና ኬክ ዝግጅት፣ በኩሊነሪ አርት፣ በምግብና መጠጥ ቁጥጥርና መስተንግዶ ዘርፎች ጥራት ያለው ተከታታይ ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። ከዚህም በተጨማሪ የሀገር በቀል ምግቦችን በሳይንሳዊ መንገድ በማጥናት ወደ ሆቴሎች የንግድ ስርአት (Menu) የማስገባት ስትራቴጂካዊ ሥራን በልዩ ትኩረት እሠራ ይገኛል። በዚህም ባለፉት 6 ወራት ብቻ 2,346 አዳዲስና ነባር ባለሙያዎችን በክህሎት ማብቃት የቻለ ሲሆን፣ ይህም የዕቅዱን 67 በመቶ መሆኑ ተመላክቷል። ይህ ስልጠና ባለሙያዎቹ በተሻለ ደመወዝ እንዲቀጠሩና የሆቴሎች አገልግሎት ጥራት እንዲሻሻል መንገድ ከፍቷል። በተመሳሳይ፣ ኩሪፍቱ ሪዞርትና ሞናርክ ሆቴልን ጨምሮ ስድስት የሚሆኑ ሆቴሎች የኢንስቲትዩቱን የጥናት ውጤት መሠረት በማድረግ ባህላዊ ምግቦችን በሜኗቸው አካተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ይህም ባህላዊ ምግብና መጠጦቻችንን ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ለማስተዋወቅና የገበያ ዕድልን ለማስፋት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል፡፡
somSOM
Scroll to Top