Mols.gov.et

በኦሮሚያ ክልል የእሴት ሰንሰለትን መሰረት በማድረግ …

March 12, 2026
በኦሮሚያ ክልል የእሴት ሰንሰለትን መሰረት በማድረግ በርካታ የሥራ ዕድሎችን ለዜጎች መፍጠር እንደተቻለ ተገለፀ የኦሮሚያ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራና የክህሎት ቢሮ፣ የከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራና ህጋዊነት ዳይሬክተር አቶ ተማም ሁሴን እንደሚገልፁት በክልሉ በዶሮ እርባታ፣ በከብት ማድለብ፣ በንብ ማነብና በመሳሰሉት ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራዞችን በእሴት ሰንሰለት የማስተሳሰርና ውጤታማነታቸውን የማረጋገጥ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች እንቁላል አስፈልፍለው የአንድ ቀን ጫጩት የሚያስረክቡ፣ የእንቁላልና ሥጋ ዶሮዎችን የሚያረቡና ለገበያ የሚያቀርቡ ኢንተርፕራይዞችን በእሴት ሰንሰለት ለማስተሳሰር በተሠሩ ሥራዎች በርካታ ቁጥር ላላቸው ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አቶ ተማም ይናገራሉ፡፡ የትስስሩን ውጤታማነት ለማረጋገጥም የብድር፣ የማምረቻና መሸጫ ቦታ አቅርቦት የማመቻቸት ሥራ በሥፋት እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን በዶሮና በከብት መኖ ምርት ላይ ለሚሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የሊዝ ፋይናንስን በመጠቀም ማሽኖች እየቀረበ እንደሚገኝም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡ በተመሳሳይ የእንስሳ መኖ ዝግጅት ጀምሮ በወተት ከብት እርባታና የወተት ተዋፅኦን አቀነባብረው ለገበያ የሚያቀርቡ ኢንተርፕራይዞችን ለማስተሳሰር እንዲቻልም የከብት እርባታ የክላስተር ማዕከላትን በሁሉም የኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች የማስፋት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም በኢንተርፕራይዝ ተደደራጅተው በወል ቦታዎች ላይ የስንዴ እያመረቱ የሚገኙ ወጣቶችን ዱቄት፣ ዳቦና ኬክ ከሚያመርቱና ለገበያ ከሚያቀርቡ ኢንተርፕራይዞች ጋር የማስተሳሠር ሥራ ለመሥራት የሚስችል ዕቅድ እየተዘጋጀ እንደሚገኝም ጠቁመዋል ፡፡ ኢንተርፕራይዞችን በግብዓትና ምርት አቅርቦት በማስተሳሰር በርካታ የሰው ኃይልን ተሳታፊ የሚደርግ የሥራ ዕድል የመፍጠር ግብ ያለው ‹‹እሴት ሰንሰለትን መሰረት ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራ›› በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በተቀረፀው የዘርፉ አዲስ እሳቤ ውስጥ ከተካተቱ ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡
somSOM
Scroll to Top