ፈጠራና ፍጥነት በታከለበት መልኩ ምርታማነትን ለማረጋገጥ በዞኑ የአመራር አቅም ግንባታ ላይ በቋሚነት ድጋፍ እናደርጋለን፡፡
August 11, 2024
ፈጠራና ፍጥነት በታከለበት መልኩ ምርታማነትን ለማረጋገጥ በዞኑ የአመራር አቅም ግንባታ ላይ በቋሚነት ድጋፍ እናደርጋለን፡፡
ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ የ2016 ዓ.ም የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በምስራቅ ሀረርጌ ዞን የማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂደዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የአቅመ ደካሞችና አረጋውያን እንዲሁም የትምህርት ቤት ማስፋፊያ ግንባታን አስጀምረዋል፡፡
ለባቢሌ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅም የተለያዩ የማሰልጠኛ እና 1000 ለሚሆኑ የዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍል ተማሪዎች የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
በባቢሌ ወረዳ ኢፋና ጃለሌ ቀበሌ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከሁለት ሺህ በላይ የተሻሻሉ የሙዝ ችግኞችን የተከሉ ሲሆን በቀጣይ 10 ሺህ የተሻሻሉ የሙዝ ችግኞችን ለመትከል ቅድመ ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀ ተጠቁሟል፡፡
በባቢሌ ከተማ አስተዳደር በተካሄደው የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ መልዕክት ያስላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈረሃት ካሚል እንደገለጹት፤ ዜጎች ሀገራቸውን እንዲያውቁ፣ አመራሩ ከህብረተሰቡ ጋር እንዲመካከርና ችግሮቹን እንዲፈታ ታሳባ በማድረግ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የመንግስት አቅጣጫ ሆኖ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል፡፡
በዚህ መሰረት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ በተለያዩ ክልሎች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
ዛሬ ያስጀመርነው መርሃ ግብር በክልሉና በዞኑ የተጀመሩ ጥረቶችን የማገዝና የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ ነው፡፡
ፈጠራና ፍጥነት በታከለበት መልኩ ምርታማነትን ለማረጋገጥ በዞኑ የአመራር አቅም ግንባታ ላይ በቋሚነት ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
ይህም ሁሉም ምርታማ የሚሆንበትን ዕድል ይፈጥራል ያሉት ክብርት ሚኒስትር በመርሃ ግብሩ የሚከናወኑ ተግባራት የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ እንዳልሆኑም ጠቁመዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወ/ሮ ሚስኪ መሐመድን ጨምሮ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የተጠሪ ተቋማቱ እንዲሁም የክልል፣ የዞንና የወረዳው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።