Mols.gov.et

የሥራ ዕድል ፈጠራን ወደ ሀብት ማፍሪያነት

July 12, 2026
‹‹የሥራ ዕድል ፈጠራን ወደ ሀብት ማፍሪያነት፣ ማኅበራዊ ተቋማትን ደግሞ ወደ ልማት ሞተርነት ለመቀየር የሁሉንም የዘርፉን አስፈፃሚ አካላት ቁርጠኝነትና ትጋት ይጠይቃል›› ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ የ2018 ዓመት አፈፃፀምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ከክልሎች ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል፡፡ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ የዘርፉን አዲስ እሳቤ መነሻ በማድረግ ለዘመናት የተጠራቀመውን ዕዳ የሚያቃልሉ፣ የዜጎችን አሁናዊ ፍላጎት የዋጁና የመጪውን ዓለም ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ያደረጉ ተግባራት በበጀት ዓመቱ መከናወናቸውን ገልጸዋል። ከእነዚህም መካከል “ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ” ቀዳሚው መሆኑን ጠቅሰው ሥራ ፈላጊዎች በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ልል ክህሎት (Soft Skills) እና ጠጣር ክህሎት (Hard Skills) ታጥቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። የቤተሰብ ቢዝነስን በማስፋፋት፣ እሴት አካይ ምርትን በማሳደግ እንዲሁም የመስሪያ፣ የመሸጫና የካፒታል አቅርቦት ችግሮችን በማቃለል ከከ4.9 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ከአዳዲስ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡ በኢኖቬሽን ላይ የተመሠረተ ስልት በመቀየስ ፈጣን የማደግ አቅም ያላቸውን ኢንተርፕራይዞች በቅርበት በመደገፍ ውጤታማነታቸውን ማረጋገጥ መቻሉን የጠቆሙት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ለመሰል ኢንተርፕራይዞች የተሰጠው ልዩ ትኩረት “ከዳቦ በላይ” የሚለውን አዲስ እሳቤ ለማሳካት ዋነኛ ስልት ሆኖ መገኘቱንም አመላክተዋል፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራን ወደ ሀብት ማፍሪያነት፣ ማኅበራዊ ተቋማትን ደግሞ ወደ ልማት ሞተርነት ለመቀየር የሁሉንም የዘርፉን አስፈፃሚ አካላት ቁርጠኝነትና ትጋት እንደሚጠይቅም በአፅንኦት አንስተዋል፡፡ የሥራና ክህሎት ዘርፍ የሀገራችንን ወደ ላቀ ብልጽግና ለማሸጋገር ያለውን አስተዋፅኦ በሚገባ በመገንዘብ የዘርፉን ተልዕኮዎች በክህሎትና ኢኖቬሽን ለመምራት ሁሉም አስፈፃሚ አካላት ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ክቡር አቶ ሰለሞን በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ አሳስበዋል፡፡
oroORO
Scroll to Top