Mols.gov.et

የሚተገበሩ አሠራሮችን ውጤታማ ለማድረግ …

July 13, 2026
የሚተገበሩ አሠራሮችን ውጤታማ ለማድረግ በፖሊሲ ንድፍና በተግባራዊ አፈጻጸም መካከል ያለውን ክፍተት መሙላት ወሳኝ መሆኑን ተመላከተ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ፐብሊክ ሴክተር ኢኖቬሽን ላብ (PSI Lab) ከአሜሪካ ኤምባሲ እና ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የአቅም ግንባታ ሥልጠና መድረክ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል። የሥልጠናው ዋና ዓላማ ሚኒስቴሩ የዘርፉ ተግዳሮቶችን በጥናትና ምርምር ታግዞ ለመፍታት ያቋቋመውን የፒኤስ አይ ላብን(PSI Lab) የውስጥ አቅም ማጠናከር፣ ተቋሙ ያቀዳቸውን ስትራቴጂካዊ ግቦች ማሳካትና ማዕከሉን ከምርምር ተቋማት ጋር ማስተሳሰር ነው ተብሏል። በዚህ መድረክ ላይ ከ8ቱ የኢትዮጵያ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎችና ከ2ቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ የአመራር አካላት እንዲሁም ከሚኒስቴሩና ከፒኤስአይ ላብ የተወጣጡ ሠራተኞችና አመራሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ የአሜሪካ ኤምባሲ ተወካይ ዶ/ር ጆን ኬለር ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኤምባሲው ባለፉት ሦስት ዓመታት 10 የሀገሪቱን የሕዝብ ምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ራስ-ገዝነት ለሚያደርጉት የሽግግር ጉዞ የፖሊሲ ሰነዶችን በማስተካከልና የአመራር አቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመስጠት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው ዩኒቨርሲቲዎች ካጋጠሟቸው ተግዳሮቶችና ስጋቶች በመነሳት፣ ከፖሊሲ ቀረጻ ባለፈ ወደ ትግበራ መሸጋገር የሚችሉበትን ክህሎት ለማስታጠቅ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸው ኃላፊነትን ወደታች ለማውረድና (Decentralized) የሚተገበሩ አሠራሮችን ውጤታማ ለማድረግ በፖሊሲ ንድፍና በተግባራዊ አፈጻጸም መካከል ያለውን ክፍተት መሙላት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል። የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሀሰን ሁሴን(ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲሁም ከፖሊቴክኒክ ኮሌጆች ጋር የተከናወኑ ሥራዎች በከፍተኛ አመራሩ ባበለቤትነት ስለተመሩ የሚታይ ውጤት ማስመዝገብ መገመራቸውን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች በተግባራዊ ምርምር ስራዎቻቸው ማኅበረሰቡንና አካባቢውን ለመለወጥ ትልቅ ተስፋ የሚጣልባቸው ተቋማት በመሆናቸው፣ ከድህነት መውጫና ወደ ብልጽግና መሸጋገሪያ መሰላል የመሆን ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። ዶ/ር ሀሰን አክለውም፤ የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ከመንግሥት በጀት የማይቀበል፣ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር ግን ሙሉ በሙሉ የመንግሥት የሆነ ራሱን የቻለ (Autonomous) ተቋም መሆኑን በመጥቀስ፣ ተሳታፊዎች ከዚህ ስኬታማ ተሞክሮ ተቋማዊ ትምህርት መቅሰም እንደሚችሉ አብራርተዋል የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የፒኤስ አይ ላብ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ጥላሁን በጅቷል በበኩላቸው፤ ሥልጠናው በሲስተም ቲንኪንግ (Systems Thinking)፣ ዲዛይን ቲንኪንግ (Design Thinking)፣ ቼንጅ ማኔጅመንት (Change Management)፣ ትራንስፎርሜሽን (Transformation) እና ስትራቴጂክ ቲንኪንግ (Strategic Thinking) ዙሪያ ላይ ያተኮረ መሆኑን አብራርተዋል። በአለም አቀፍ አሰልጣኞች ድጋፍ የሚሰጠው ይህ ስልጠና የሚከታተሉ ሰልጣኞች ሥልጠናውን ሲያጠናቅቁ በየተቋማቸው የሚተገብሯቸውን የስትራቴጂክ ዕቅዶችና የተለያዩ የስትራቴጂካዊ ፕሮፖዛሎችን ያዘጋጃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
oroORO
Scroll to Top