Mols.gov.et

በጋራ እንፈጥራለን

July 2, 2026
በጋራ እንፈጥራለን የሥራና ክህሎት ሚንስቴር ተጠሪ ተቋም የሆነው የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የሚያዘጋጀው የቴክኖሎጂ ባህል ግንባታ ፓነል ውይይት ለአምስተኛ ዙር «በጋራ እንፈጥራለን» በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል። የኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጸዳለ ተክሉ እንደገለጹት፤ ይህ የፓናል ውይይት በቡድን ስራ ውጤታማነት ላይ ያተኮረ ምክረ-ሀሳብ ለመለዋወጥ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል። ስለ ኢኖቬሽንና ፈጠራ ሲነሳ የቡድን ስራ ወሳኝ ተግባር መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ኢንስቲትዩቱ ለፈጠራ ባለሙያዎች አርአያ እንዲሆን የተለያዩ ዘርፎች እርስበርስ መተሳሰር እንዳለባቸውና በዘርፉ ያሉ በርካታ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን ለማሳካት የቡድን ስራ የግድ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። በተጨማሪም በጋራ መስራት እውቀትን፣ ክህሎትን እና ችሎታን በማቀናጀት የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ አዳዲስ ግኝቶችን ለመፍጠር እንደሚያስችል አብራርተዋል። በመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር ላይ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆኑት ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች የዕለቱ የፓናል ውይይት ዋና ተሳታፊዎች የነበሩ ሲሆን በጋራ መስራታቸው ለፈጠራ ስራቸው ያበረከተውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለታዳሚ ወጣቶች ልምዳቸውን አካፍለዋል። ወጣቶቹ ሀመረ፣ ሩት፣ ያብስራ እና ሪሃና “የተንቀሳቃሽ የአእምሮ ግፊት መከላከያ መሳሪያ” ላይ ያመጡትን አዲስ የፈጠራ ስራ በሂደቱ የገጠሟቸውን ተግዳሮቶች እና በጋራ ያሳለፉትን ጠንካራ ተሞክሮ አቅርበዋል። እነዚህ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ወደፊትም ፕሮጀክታቸውን ይበልጥ በማሳደግ ወደ ምርት ለማሸጋገር እና ለሀገራችን የጤና ዘርፍ ትልቅ መፍትሄ ለማምጣት በርትተው እንደሚሰሩ በቁርጠኝነት ገልጸዋል። በሌላ በኩል በኢንስቲትዩቱ የሊደርሽፕና ማኔጅመንት ፋኩልቲ አማካኝነት በቡድን ስራ ውጤታማነት፣ ተግዳሮቶች እና ሊከተሏቸው በሚገቡ ስልታዊ አካሄዶች ላይ ያተኮረ መወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል። በቡድን መስራት በዘላቂነት ትርፋማ እንደሚያደርግ የተገለጸ ሲሆን ከታዳሚዎች ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችም ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል። በአጠቃላይ በኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂና ፈጠራ ባህልን ለማስረጽ የተጀመረው ይህ የፓነል ውይይት መድረክ በየጊዜው ሰፊና በጎ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ አዳዲስ ሀሳቦች እየተገኙበት መሆኑ ተመላክቷል። መረጃው የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢኒስቲትዩት ነው፡፡
oroORO
Scroll to Top