በመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ የፈጠራ ባለሙያዎች ከፍተኛ ውጤ
June 15, 2026
በመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ የፈጠራ ባለሙያዎች ከፍተኛ ውጤት አስመዘገቡ
በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር በተዘጋጀው የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቴክኒክና ሙያ የጥናትና ምርምር ጉባኤ እና የቴክኖሎጂ ውድድር፣ ኢትዮጵያውያኑ የፈጠራ ባለሙያዎች አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቀዋል።
ከሰኔ 5 ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው በዚህ መድረክ ከ10 አገራት የቀረቡ 35 የፈጠራ ሥራዎች ውስጥ 6ቱ ለፍጻሜ የደረሱ ሲሆን፣ 4ቱ ከኢትዮጵያ፣ 1 ከሕንድ እና 1 ከናይጄሪያ ነበሩ።
በመጨረሻው ውድድር የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ግብርናን ለማጎልበት የሚያስችል በIoT ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የመስኖ ክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ያቀረበው ዘላለም እንዳለው አንደኛ ደረጃን በመያዝ የዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
አካልን ሳይጎዳ የጭንቅላት ውስጥ ግፊትን ለመለካት የሚያስችል CEREBRO-LOGIC የተሰኘ ፈጠራ ያቀረቡት ሩት ጌታቸው፣ ሀመረ፣ ያብስራ እና ሪሀና ሁለተኛ ደረጃን በማግኘት የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።
ከናይጄሪያ የቀረበው የገቢ መረጃና ተከታታይነት ማረጋገጫ ሥርዓት (Revenue Intelligence and Traceability System) ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን በማግኘት የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር ለአሸናፊዎቹ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት፣ ውጤቱ የኢትዮጵያ ወጣቶች በምርምር፣ በክህሎትና በፈጠራ ያላቸውን አቅም በግልጽ ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
የፈጠራ ሥራዎቹ ከውድድር ባሻገር ወደ ሥራ እና ወደ ገበያ እንዲገቡ አስፈላጊ ድጋፎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በማጠቃለያው ሥነ ሥርዓት ላይ ለሁሉም ተወዳዳሪዎች የምስክር ወረቀት የተበረከተ ሲሆን፣ ለአሸናፊዎችም እንደየደረጃቸው ሜዳሊያና ልዩ ሽልማቶች ተሰጥተዋል።


