ኮሌጁ በዘርፉ የተደረገው ሪፎርም ተጨባጭ ውጤት እንዲያስመዘግብ …
May 21, 2026
ኮሌጁ በዘርፉ የተደረገው ሪፎርም ተጨባጭ ውጤት እንዲያስመዘግብ ያስቻለው መሆኑን አስታወቀ
በአዲስ አበባ የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በዘርፉ የቀረፀውን የሪፎርም አጀንዳ ወደ መሬት በማውረድ ተጨባጭ ሽግግር ውጤቶች ማስመዝገቡን አስታውቋል።
ኮሌጁ ባወጣው መረጃ፤ ስልጠናን ከገበያ ፍላጎትና ከተግባራዊ የኢንተርፕራይዝ ድጋፍ ጋር በማጣመር የተከናወኑ ተግባራት የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን አቅም በመገንባት፣ ወደ መካከለኛና ከፍተኛ አምራችነት እያሸጋገረ ይገኛል።
የኮሌጁ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ምክትል ዲን አቶ ታከለ ኩሙላ እንደገለጹት፤ ተቋሙ የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን በቀጥታ ከኢንዱስትሪዎች እና ከኢንተርፕራይዞች ተጨባጭ ፍላጎት በመነሳት እየሰራ ይገኛል።
በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ አስር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ሰርቶ ማሸጋገር መቻሉን ተመላክቷል፡፡
ኮሌጁ ባደረገው የውጤት ዳሰሳ ጥናት፤ ባለፈው ዓመት የተሸጋገሩ ቴክኖሎጂዎች ለኢንተርፕራይዞች ከ749 ሺህ ብር በላይ አዲስ ሀብት ማፍራት አስችለዋል፡፡ ይህንን ውጤት እስከ በጀት ዓመቱ ማብቂያ ድረስ ወደ አንድ ሚሊዮን ብር ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝም ነው የተገለፀው፡፡
ኮሌጁ የስልጠናና ድጋፍ ስራዎቹን ከግል ተቀጣሪነት ወደ ስራ ፈጣሪነት በሚያሸጋግሩ የተግባራዊ ኢንኩቤሽን ማዕቀፎች ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡
አሁን ላይ ኮሌጁ ለይቶ ከሚደግፋቸው 859 ኢንተርፕራይዞች መካከል 243ቱ ቀጣይነት ያለው የካይዘን፣ የቢዝነስ ማኔጅመንት እና የማርኬቲንግ ድጋፍ በየሳምንቱ እንደሚያገኙም የኮሌጁ መረጃ ያመለክታል።
ኮሌጅ በወጣው መረጃ፤ የዘርፉ አዲስ እሳቤ ሀገራዊ ምርትን ከማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሬን ከመተካት እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ ተጨባጭና አመርቂ ውጤት እያመጣ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ስትራቴጂውን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡







