ትውልዱ በቴክኒክና ሙያ. . .
April 30, 2026
ትውልዱ በቴክኒክና ሙያ ያገኘውን ክህሎት ለእድገት በተግባር መተርጎም ይጠበቅበታል
ትውልዱ በቴክኒክና ሙያ መስክ የሚያገኛቸውን ክህሎቶች በተግባር በመተርጎም ለእድገት የበኩሉን ሚና ሊጫወት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ገለጸ።
የተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የ100ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ በዓል የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት “ዘመን ተሻጋሪ ቅርስ ለቀጣዩ ትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች አከብሯል።
በሥነ-ሥርዓቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጁ መምህራንና ተማሪዎች፣ የቀድሞ ተማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በመድረኩ በኮሌጁ የተሰሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አውደ-ርዕይ፣ የኪነ-ጥበብ ስራዎችና የባህል አልባሳት ትዕይንት ቀርበዋል።
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ሚደቅሳ ከበደ በዚሁ ወቅት፤ የከተማ አስተዳደሩ የገበያውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ብቁ ሙያተኛ ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ሰልጣኞች በቂ ክህሎት እንዲጨብጡ ከኢንዱስትሪዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ከቴክኖሎጂ ዕውቀት ውጪ ልማትና ዕድገት ማረጋገጥ እንደማይታሰብ ጠቁመው፤ በዚህ በኩል ተማሪዎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በብቃት ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በዓሉን ከማክበር ባለፈ በቴክኒክና ሙያ መስክ የታነፀ ትውልድ ለማፍራት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።


