የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አገልግሎትን ለማሻሻል …
November 4, 2026
የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አገልግሎትን ለማሻሻል የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ
የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ሂደትን ይበልጥ ቀልጣፋ፣ ግልጽና ፍትሐዊ ለማድረግ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት ማጠናከርና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሠራርን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍና ለዜጎች ቀልጣፋና ፍትሐዊ አገልግሎት መስጠት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ የዘርፉን አሠራር ለማሻሻል፣ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍና ግልጽነትን ለማረጋገጥ በተቋማትና በባለድርሻ አካላት መካከል የተቀናጀ አሠራር መፍጠር ቁልፍ የትኩረት መስክ መሆኑ ተጠቁሟል።
ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት አግኝተው ሕጋዊና ደህንነቱ የተጠበቀ የውጭ ሀገር የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የመንግሥትና የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ ዲጂታል አሠራሮችን ማጠናከር የአገልግሎት አሰጣጡን ግልጽና ቀልጣፋ ከማድረጉም በላይ የአሠራር መጓተትን ለመቀነስ፣ ተጠያቂነትን ለማሳደግና ዜጎች በተሻለ ሁኔታ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያግዝ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡
በውይይቱ የጉዞ ወኪል ማህበራትና የቦርድ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡




