የሥልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ የአሰልጣኞች አቅም ግንባታ ወሳኝ ነው
November 4, 2026
የሥልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ የአሰልጣኞች አቅም ግንባታ ወሳኝ ነው፡፡
ክቡር ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር)
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና በኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ኢኒስቲትዩት ትብብር በሥስት ዙሮች በተለያዩ ከተሞች ሲሰጥ የነበረው የፋውንዴሽን ክህሎት የአሰልጣኞች ስልጠና የማጠናቀቂያ መርሃግብር ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፉን ለማሻሻልና ለማሳደግ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲውን ከማሻሻል ጀምሮ አዲስ ስትራቴጂ ተቀርጾ በእነሱም ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥና የማወያየት ስራዎች መሰራታቸውን አውስተዋል፡፡
የሥልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ የአሰልጣኞች አቅም ግንባታ አንዱና ዋነኛው በመሆኑ ባለፉት ዓመታት ብዙ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
የቴክኒካል ክህሎት ክፍተቶችን በመለየት በተሰጡ ስልጠናዎችም ለውጥ ማግኘት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ የተገኘው ክፍተት የልል ክህሎት (soft skills) በመሆኑ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አንድ ዜጋ ቴክኒካል ክህሎት ስላለው ብቻ ተወዳዳሪ መሆን ስለማይችል ዜጎች ለሁሉም ነገር ዝግጁ እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ከዚህ ዓመት ጀምሮ ሰልጣኖች ይህንን የልል ክህሎት ስልጠና በትምህርታቸው ተካቶ እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህም አሰራር ግዴታ በመሆኑ ሰልጣኞች የማስፈጸም ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በቀጣይም ስልጠናውን ከላይኛው መዋቅር ጀምሮ እስከ ክላስተር ደረጃ ማስፋፋት እንደሚጠበቅ በመግለጽ፣ በእስካሁኑ ሂደት አበርክቶ ለነበራቸው አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ደ/ር ሐሰን ሁሴን በበኩላቸው፤ የዚህ ስልጠና ዋና አላማ ለተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለማህበረሰቡም አርአያ የሚሆን ዜጋ መፍጠር ነው ብለዋል፡፡
ልጣኞችም በሙያቸው ለተማሪዎችና ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ እንዲሁም ዜጎችን መለወጥ የሚችሉ እንዲሆኑ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ያላት ትልቁ ሀብት ወጣት በመሆኑ እነሱን ለአለም ተወዳዳሪ አድርጎ የማውጣት እና የነገውን የኢንተርፕራይዝ ማስፋፊያ አሻራ የማሳረፉ ኃላፊነት በእጃቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ተሳታፊዎችም በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህን መሰል ስልጠና በማዘጋጀቱ ደስታቸውን ገልጸው የተሰጣቸው ኃላፊነት ትልቅ መሆኑን በመገንዘብ የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡















