ወጣት ሴቶች የሚሳተፉበት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን የፈጠራ ሃሳብ ውድድር በይፋ ተጀመረ፡፡
October 9, 2024
ወጣት ሴቶች የሚሳተፉበት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን የፈጠራ ሃሳብ ውድድር በይፋ ተጀመረ፡፡
ውድድሩ ‹‹ስታርታፕ ፋውንደርስ የአይሲቲ ኢኖቬሽን›› በሚል ስያሜ ነው የሚካሄደው፡፡
የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ዲጂታላይዜሽን ከዓለም ጋር ያለንን ተወዳዳሪነት የሚወስንበት ጊዜ ላይ የምንገኝ እንደመሆኑ መንግስት ልዩ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች መካከል ቀዳሚው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርም የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ፈጠራ አማራጭ መሆኑ እና ሚኒስቴር መ/ቤቱ በሚያስፈፅማቸውን ተልዕኮዎች በውጤታማነት ለማሳካት ያለውን ሚና ከግምት በማስገባት ዲጂታላይዜሽንን የሚያሳድጉ ተግባራትን በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
ወጣት ሴቶች የፈጠራ ዕምቅ አቅማቸውን ተጠቅመው የማህበረሰባቸውን ችግሮች መፍታት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ማመንጨት የሚያስችላቸውን ዕድል ለመፍጠር ውድድሩ መዘጋጀቱን ኩቡር ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡
የሴቶች ስታርታፕ ፋውንደርስ ፕሮግራም በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም በኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢኒስቲትዩት ትብብር እ.ኤ.አ ከ2023 ጀምሮ እየተተገበረ የሚገኘው የኔክስት ኢትዮጵያ ስታርታፕ (NEST) አካል መሆኑን የገለፁት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ትራንስፎርሜሽን ውስጥ ስታርታፕ ቢዝነስ አንቀሳቃሾች የራሳቸውን ድርሻ የሚወጡበት ሥነ ምህዳር የመፍጠር ዓላማን እንደያዘም አስረድተዋል፡፡
‹‹የሴት ስታርታፕ ፋውንደርስ የአይሲቲ ኢኖቬሽን›› ውድድር ለሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የውድድሩ አሥር አሸናፊዎች የአንድ መቶ ሺ ብር ተሸላሚ ይሆናሉ፡፡