Mols.gov.et

በ27 ከተሞች ከ1መቶ ሺ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ …

June 13, 2026
በ27 ከተሞች ከ1መቶ ሺ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የፕሮግራም ማሻሻያ ይፋ ሆነ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የወጣቶች የሥራ ልምምድ ፕሮግራም በሆነው «ብቃት» እና «የሥራ ማዕከላት አገልግሎት ማሻሻያ » ፕሮግራሞችን በአዳዲስ ከተሞች ለማስፋት የሚያስችል የማብሰሪያ መድረክ አካሂዷል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ የሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት፣ ከ18-25 የሆኑና የትምህርት ደረጃቸው 12ኛ ክፍልና ከዚያ በታች የሆኑ ሥራ ፈላጊ ወጣቶችን ሕይወት በመለወጥ ረገድ የ«ብቃት» ፕሮግራም ከፍተኛ ስኬት አስመዝግቧል፡፡ እስካሁን 93 ሺህ 665 የሚሆኑ ወጣቶች የሕይወት ክህሎት ሥልጠና ያገኙ ሲሆን 54 ሺህ 913 ወጣቶች ደግሞ የስድስት ወር የተግባር ልምምዳቸውን አጠናቀዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 52 ሺህ 786 የሚሆኑት ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ከተጠቃሚዎቹ መካከልም 67.6 በመቶ ያህሉ ወጣት ሴቶች መሆናቸው ፕሮግራሙ ማኅበራዊ ፍትሐዊነትን በግልፅ ያመላከተ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ በሌላ በኩል “የሥራ ማዕከላት አገልግሎት ማሻሻያ” ፕሮግራም ባለፉት ዓመታት በአምስት ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ 18 የሥራ ማዕከላት ዕድሳት ተደርጎላቸው የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስ የተሟላላቸው ሲሆን አገልግሎታቸውንም ከኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ጋር የማቀናጀት ሰፊ ሥራ ተከናውኗል፡፡ ከዓለም ባንክ በተገኘ የ52 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ፋይናንስ የ«ብቃት» ፕሮግራም ተጠቃሚ ከተሞች ቁጥር ከ11 ወደ 27 ለማስደግ መቻሉን፣ ብሎም በሚቀጥሉት 2 ዓመታት ውስጥም ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 29 የሆኑ 100,000 አዳዲስ ወጣቶች ተጠቃሚ እምደሚሆኑ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ይፋ አድርገዋል፡፡ ወደ ፕሮግራሙ አዲስ ከሚገቡት 16 ከተሞች መካከል ሰበታ፣ ቡራዩ፣ ቢሾፍቱ፣ አሰላ፣ አምቦ፣ ነቀምት፣ አርባ ምንጭ፣ ሆሳዕና፣ ዲላ፣ ደሴ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ታቦር፣ ደብረ ብርሃን፣ ሽሬ እንዳሥላሴ፣ ጅጅጋ እና ሐረር እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል በ«የሥራ ማዕከላት አገልግሎት ማሻሻያ»ፕሮግራም አማካኝነት በሁሉም ክልሎች በሚገኙ 88 የምግብ ዋስትና ፕሮጀክት በሚተገበርባቸው ከተሞች ውስጥ ተጨማሪ 200 የሥራ ማዕከላት የአቅም ግንባታ ድጋፍ ያገኛሉ። እነዚህ ማዕከላት የቢሮ መገልገያ መሣሪያዎች ተሟልተውላቸው አገልግሎታቸው ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝድ የሚደረግ ሲሆን የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓትንም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚያደርጉም ተመላክቷል፤ አዳዲስ ወደ ፕሮግራሙ የሚገቡ ከተሞች ከነባሮቹ ተሞክሮ በመውሰድ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ፤ እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አመራሮች፣ ከንቲባዎችና ባለድርሻ አካላት ለፕሮግራሞቹ ውጤታማነት ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
oroORO
Scroll to Top