Mols.gov.et

በአፍሪካ የወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ ከሁሉም ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባል፡፡ ክቡር አቶ አደም ፋራህ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት

July 9, 2025
በአፍሪካ የወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ ከሁሉም ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባል፡፡ ክቡር አቶ አደም ፋራህ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ላለፉት ሦስት ተከታታይ ቀናት በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ሲካሄድ የቆየው 3ኛው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም በስኬት ተጠናቋል፡፡ በማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ ከኢትዮጵያ እና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ሚኒስትሮች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡ በፎረሙ ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት አቶ አደም ፋራህ በርካታ በአምራች የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ወጣት የሚገኝባት አፍሪካ ወጣቱ ላይ ኢንቨስት ማድረግና የሥራ ዕድል መፍጠር የአህጉሪቱ ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ በወጣቱ ላይ ኢንቨስት አድርጎ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ የመንግስት አቅም እንዳለ ሆኖ የግሉ ሴክተር፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ወጣቶች እራሳቸው እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሳተፉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሁሉአቀፍ እና አካታች የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ በዘርፉ የሚሰሩ ሥራዎች ገጠርና ከተማ፣ ወጣቶችን፣ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞችን ያካተቱ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚንስትር ክብርት ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው ፎረሙ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የፖሊሲ ግብዓቶች የተገኙበት፣ ቀጣይ በአህጉሪቱ በዘርፉ በሚከናወኑ ጉዳዮች ላይ የጋራ ውሳኔዎች የተላለፉበት፣ የተሞክሮ ልውውጥ የተካሄደበት፣ ቀጠናዊ ውህደትን ማፋጠን በሚያስችል መልኩ በትብብር እና በትኩረት ለመስራት ከስምምነት የተደረሰበት ፍሬያማ መድረክ ነበር ብለዋል፡፡ አክለውም በቀጣይ መድረኩ በዘርፉ ትላልቅ ውሳኔዎች ተላልፈው እንዲተገበሩና የሀገራት መሪዎች እንዲሳተፉበት በጉባኤ ደረጃ እንዲቀጥል የጋራ ስምምነት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ በመድረኩ ማጠቃለያ በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ በአመቱ ጉልህ አበርክቶ የነበራቸው ተቋማት፣ ሞዴል ኢንተርፕራይዞች፣ የሥራ ማዕከላት እና የፋይናንስ ተቋማት እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ሚንስትሯ ፎረሙ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ተቋማት፣ ግለሰቦች እና ተባባሪ አካላት በሙሉ አመስግነዋል፡፡ #AJCF2025, #Jobs4Africa, #AfCFTA, #DigitalInclusion, #YouthEmployment ሐምሌ 2/2017 ዓ.ም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
oroORO
Scroll to Top