ሚኒስቴሩ ከኦሮሚያ ባንክ ጋር…
April 16, 2026
ሚኒስቴሩ ከኦሮሚያ ባንክ ጋር የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ተፈራረመ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ባንክ ጋር በመተባበር በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በክህሎት ልማትና በፋይናንስ አቅርቦት ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ 70 በመቶው ወጣት ያለባት ሀገር እንደመሆኗ፣ ይህን የሰው ኃይል ወደ ስራ ለማሰማራት የፋይናነስ ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው።
ኦሮሚያ ባንክ ራሱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያደራጀ መሆኑ ከሚኒስቴሩ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት (LMIS) ጋር ተዳምሮ ወጣቶች በቀላሉ የብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ባንኮች ስለ ስልጠና ሳይጨነቁ ሚኒስቴሩ በየደረጃው ባሉ መዋቅሮቹ ያሰለጠናቸው “እጃቸው ለሥራ የተፍታታ” ዜጎችን ያቀርባል ያሉት ክብርት ሚኒስትር ይህንን መነሻ በማድረግ የኦሮሚያ ባንክ የዲጂታል ብድር አሰራር ከሚኒስቴሩ ቴክኖሎጂዎችና መዋቅሮች ጋር ተሳስሮ ከቅድመ ብድር እስከ ማስመለስ ያለውን ሂደት በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
የርቀት ሥራ ፣ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር የሥራ ዕድሎችን በጋራ ከመስራ ባሻገር ለየት ያለ ክህሎት ያላቸው የወጣቶችን ተሰጥኦ በመመንዘር ወደ ሀብት መቀየር የሚያስችሉ ስራዎች በትብብር እንደሚሰራም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ተፈሪ መኮነን በበኩላቸው፣ ሚኒስቴሩ በቴክኖሎጂ የታገዘና ከዘመኑ ቀድሞ የሚራመድ ሥራ እየሰራ መሆኑን አድንቀዋል።
ባንካቸው ማህበረሰብ ተኮር በመሆኑ፣ ይህ ስምምነት በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ሕይወት ለመቀየር ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ ከሚናገረው በላይ በተግባር እጅግ አስደናቂ ሥራዎችን እየከወነ መሆኑን በአካል ተመልክተናል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው እኛም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የብድር ሥርዓታችንን በመጠቀም፣ ወደ ውጭ ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎችን ጨምሮ የሁሉንም ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።





