የ2016 ዓ.ም የሥራ ጉባኤ እና ኢትዮጵያ የዓለም የሥራ ድርጅትን…
November 30, 2023
“ጉባኤው አሠሪው፣ ሠራተኛና መንግስት በጋራ የሚመካከሩበት እና ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሰላም ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ የሚፈጠርበት ነው፡፡”
ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
የሥራና ክህሎት ሚንስትር
የ2016 ዓ.ም የሥራ ጉባኤ እና ኢትዮጵያ የዓለም የሥራ ድርጅትን የተቀላቀለችበት መቶኛ ዓመት ክብረ በዓል አስመልክቶ ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የዓለም የሥራ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ኮንፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ የሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ከህዳር 24-26/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄደው ኮንፈረንስ አስመልክቶ የሥራና ክህሎት ሚንስትር ክብርት ሙፈሪሃት ካሚል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት ጉባኤው ስለ አሠሪው እና ሠራተኛው አብረን የምንመክርበት፣ የጎደለውን የምንሞላበት፣ ያለውን የምናጠናክርበት፣ እንዲሁም ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሰላም ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ የሚፈጠርበት ነው፡፡
ከዚህ ባለፈም ኮንፈረንሱ ከዓለም የሥራ ድርጅት ጋር ያለንን ትብብር የምናጠናክርበት፣ የመጣንበትን ርቀት የምንፈትሽበት፣ ስኬቶቻችንና ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች የምንፈታበት፣ ድሎቻችንን የምናከብርበት፣ በሂደቱ አዎንታዊ ሚና ሲጫወቱ የነበሩትን አካላት እውቅና የምንሰጥበት እና ለቀጣይ ጉዟችን ስንቅ የምንሰንቅበት ይሆናል ብለዋል፡፡
የዓለም ሥራ ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተር እና የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተወካይ ክቡር አሌክስዮ ሙሲንዶ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት የዓለም ሥራ ድርጅትን በመቀላቀል ከቀዳሚዎቹ አንዷ መሆኗን ገልጸው የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ፣ ጾታዊ ትንኮሳ፣ ህገ-ወጥ ስደትን መከላከል የመሳሰሉት ተግባራት በድርጅቱ የወጡ ህጎች ወስዳ በመተግበር ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡
ጉባኤው ማህበራዊ ፍትህ በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ዙሪያ ይምንመክርበት እና በቀጣይ ስለምናከናውናቸው ተግባራት በጥልቀት የምንወያይበት እና አቅጣጫ የምናስቀምጥበት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
የጋዜጣዊ መግለጫን በጋራ የሰጡት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ኮንፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ የሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን የሥራ ኃላፊዎች በጉባኤው አሠሪና ሠራተኛ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጉዳይቾ ጎልተው የሚወጡበት እና ምርታማነትን በሚያረጋግጡ ጎዳዮች ላይ መክረን የምንግባበት ይሆናል ብለዋል፡፡