የኢንተርፕረነርሺፕ ሥነ-ምህዳሩን ለማስፋት …
May 20, 2026
የኢንተርፕረነርሺፕ ሥነ-ምህዳሩን ለማስፋት የሚደረገውን ጥረት የሚያሳድገው የፐብሊክ ሰርቪስ ኢኖቬሽን ማዕከል ሥራ ጀመረ
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ሙፈሪሃት ካሚል፣ የኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ያስገነባውን የፐብሊክ ሰርቪስ ኢኖቬሽን ማዕከል መርቀው በይፋ ወደ ሥራ አስገብተዋል።
ማዕከሉ በሀገሪቱ የሥራ ፈጠራ ሥነ-ምህዳሩን ለማስፋትና የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን በፈጠራ ለማዘመን የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያግዝ ተገልጿል።
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ክብርት ሚኒስትር እንደገለፁት፤ ማዕከሉ ለፈጠራና አዳዲስ እሳቤዎች መፈለቂያ የሚሆን ነጻና ምቹ ከባቢን ይፈጥራል።
ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ላለፉት ዓመታት በኢንተርፕረነርሺፕ ሥነ-ምህዳር ግንባታ ላይ ደማቅ አሻራ እያሳረፈ መሆኑን አውስተው ወደ ሥራ የገባው ማዕከል ዜጎች ለሀገር የሚጠቅሙ አዳዲስ መፍትሄዎችን በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ እንዲያፈልቁ ሰፊ ዕድል እንደሚከፍት ጠቁመዋል።
“ለሃሳብ ክብር ሲሰጥ ሀገር በፈጠራ አቅሞች ይጥለቀለቃል፣ ሀገርም ያድጋል” ያሉት ክብርት ሚኒስትር፣ መንግስት የብሔራዊ ኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ፖሊሲን በማጽደቅ ሥነ-ምህዳሩን ለመገንባት የወሰነው የሃሳብን ክቡርነት በመገንዘብና ዘርፉን በህጋዊ ማዕቀፍ ለመምራት ካለው ጽኑ ቁርጠኝነት የተነሳ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሀገር የሚቀይር ሃሳብ ይዘው የሚለፉ ዜጎችን በተቋም ደረጃ መደገፍ መቻሉ፣ ባለሙያዎቹ የበለጠ እንዲበረቱና እንዲነቃቁ ትልቅ አቅም እንደሚሆንም አክለዋል።
ተቋሙ ተደራሽነቱን በማስፋት ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ጭምር በትብብር ለመስራት በትኩረት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አመላክተዋልዋል። ይህም ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ የምታከናውናቸው ስራዎች ቀጣናዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ያሳያል።
የሀገሪቱ የፈጠራ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የክህሎት ልማት ጥረቶች ሁሉ እርስ በርስ ተሰናስለው የኢትዮጵያን የብልጽግና ራዕይ እውን ማድረግ እንዲችሉ፣ ሁሉም ዜጋና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።








