Mols.gov.et

ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ ስታርትአፖችን …

May 21, 2026
ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ ስታርትአፖችን በሳይንሳዊ መንገድ መደገፍ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኤስ ኤንቪ ሊዌ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የብሩህ ኢትዮጵያ 2025 የስታርትአፖች ቡትካምፕ የግምገማ እና የዕቅድ ማረጋገጫ መድረክ ተካሄደ። በመድረኩ ላይ የሥራ ፈጣሪዎችን ተወዳዳሪነትና ክፍተቶች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ሳይንሳዊ ጥናት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ እንደገለጹት፤ ከማክሮ ኢኮኖሚ ዋና ዋና ፈተናዎች መካከል አንዱ የሆነውን ሥራ አጥነት በዘላቂነት ለመቅረፍ ስታርትአፖችን በሳይንሳዊ መንገድ መደገፍና ምቹ ሥነ-ምህዳር መፍጠር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም፣ በኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት (EDI) በተጠናው ጥናት መሠረት ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ እና ለአገር ውስጥ ገበያ ተግባራዊ መፍትሔ ይዘው የቀረቡ ስታርትአፖችን የፋይናንስ ተቋማት በባለቤትነት ሊደግፏቸው እንደሚገባ አሳስበዋል። ተቋማቱ ለሥራ ፈጣሪዎች አስፈላጊውን የብድርና የፋይናንስ አቅርቦት በማመቻቸት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል። የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት (EDI) ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦሩ ሸና በበኩላቸው፣ ጥናቱ ስታርትአፖች ከቡት ካምፕ ስልጠና በኋላ ቢዝነሳቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር ያሉባቸውን ተጨባጭ ክፍተቶችና ፍላጎቶች ለመለየት ታስቦ የተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል። በመድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት እንደጠቆሙት፤ በአሁኑ ወቅት ለስታርትአፖች ዕድገት ማነቆ የሆኑትን የፋይናንስ አቅርቦት፣ የሥራና ማምረቻ ቦታ፣ የገበያ ትስስር እና የብድር ዋስትና የመሳሰሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍና ምቹ የፈጠራ ሥነ-ምህዳር ለመገንባት የሁሉንም አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ ይጠይቃል። ውድድሩን በፋይናንስ የደገፈው SNV በቀጣይም የፋይናንስ፣ የቢዝነስ ልማት (BDS) እና ሌሎች ዘርፈ-ብዙ ድጋፎችን ማድረጉን የሚቀጥል ሲሆን፤ ሚኒስቴሩም የስታርትአፕ አዋጅን እና የ”ዲጂታል ኢትዮጵያ” ስትራቴጂን ስኬታማ ለማድረግ ከፖሊሲ አውጪዎች፣ ከፋይናንስ ተቋማትና ከአለም አቀፍ አጋሮች ጋር ያለውን ስልታዊ ቅንጅት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
en_USEN
Scroll to Top