Mols.gov.et

በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ኢንተርፕራይዞችን ማቋቋም …

April 22, 2026
በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ኢንተርፕራይዞችን ማቋቋም ለሥራ ባህል ግንባታ መሠረት እየጣለ መሆኑ ተገለጸ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማትን የኩባንያዎች መፈልፈያ ለማድረግ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቀረፀውን አዲሱን የሪፎርም እሳቤ መነሻ በማድረግ፣ በርካታ ተቋማት ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም የሰልጣኞችን የሥራ ባህልና ክህሎት እያሳደጉ መሆኑ ተመላከተ። የአማራ ክልል የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ስቡህ ገቢያው(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ እነዚህ ኢንተርፕራይዞች ሰልጣኞች ተግባራዊ ሥልጠናን በተጨባጭ ከማግኘታቸው ባለፈ፣ ጠንካራ የሥራ ባህል እንዲያዳብሩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። ሰልጣኞች በተጨባጭ እያመረቱ የሚማሩ መሆኑ የጊዜ አጠቃቀምን፣ ሥራን በአግባቡ መፈፀምን፣ እንዲሁም ኃላፊነትና ተጠያቂነትን በተግባር እንዲለማመዱ ዕድል እየፈጠሩላቸው መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል። ዶ/ር ስቡህ አክለውም፣ ይህ አሠራር ሰልጣኞች በሥራ ቦታ የሚፈለገውን የዳበረ ሥነ-ምግባር እንዲያጎለብቱ ከመርዳቱም በላይ፣ በቡድን የመሥራት፣ የመግባባትና የመተባበር ክህሎታቸው እንዲያድግ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። እነዚህ እሴቶች ሰልጣኞች ወደፊት ወደ ሥራው ዓለም ሲሰማሩ በቀላሉ እንዲላመዱና ውጤታማ እንዲሆኑ አስተማማኝ መሠረት ይጥላሉ። በኮሌጆች ውስጥ የሚቋቋሙ ኢንተርፕራይዞች የሰልጣኞችን የኢንተርፕርነርሽፕ አስተሳሰብ (Entrepreneurial mindset) በማሳደግ ረገድ ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ስቡህ፤ ሰልጣኞች የገቢና ወጪ ቁጥጥርን እንዲሁም የገበያ ትስስርን በተግባር እንዲያውቁ በማድረግ የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠር ያላቸውን ተነሳሽነትና በራስ መተማመን እንደሚያሳድጉት ጠቁመዋል። ይህም ጥራትን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት ላይ በማተኮር በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ የመሆን አቅምን ይፈጥርላቸዋል ብለዋል። በአጠቃላይ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ውስጥ ኢንተርፕራይዞችን ማቋቋም ሰልጣኞችን ከንድፈ-ሀሳብ ባለፈ ለተግባራዊ ዓለም የሚያዘጋጅ ስትራቴጂ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top