በክልሉ ከ517 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ባለሃብትነት ተሸጋግረዋል። የአማራ ክልል ሥራና ስልጠና ቢሮ
April 28, 2025

በክልሉ ከ517 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ባለሃብትነት ተሸጋግረዋል።
የአማራ ክልል ሥራና ስልጠና ቢሮ
በአማራ ክልል ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግስት ባደረገላቸው ድጋፍ ከ517 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ ታዳጊና መካከለኛ ባለሃብትነት መሸጋገራቸውን የክልሉ ሥራና ስልጠና ቢሮ ገለፀ።
የክልሉ ሥራና ስልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አማረ አለሙ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በክልሉ ከ517 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 345 አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ ታዳጊና መካከለኛ ባለሃብትነት ተሸጋግረዋል።
ኢንተርፕራይዞቹ ባለፉት ዓመታት በተደረገላቸው የተጠናከረ የመንግስት ድጋፍ በየተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመው ከ10ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የሥራ እድል ፈጥረዋል ብለዋል።
በቀጣይም መንግስት ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ በማመቻቸትና የገበያ ትስስር በመፍጠር ኢኮኖሚውን እንዲያነቃቁ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን የሀርቡ ከተማ ነዋሪ ወጣት መሀመድ ሰይድ እንዳለው፤ መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ባደረገለት ድጋፍ በተሰማራበት የብረታ ብረት ሥራ ውጤታማ መሆን ችሏል፡፡
ተሸከርካሪዎችን በመጠገን፣ መለዋወጫዎችን በመተካትና በሌሎችም የብረታ ብረት ሥራዎች ከመስራት ባሻገር ለ31 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩን ገልጿል።
አሁን ላይ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ ወደ ታዳጊና መካከለኛ ባለሃብትነት መሸጋገሩ እንዳስደሰተው አስረድቷል።
ሌላው በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የከሚሴ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሰይድ እንድሪስ በበኩሉ ባለፉት ዓመታት በቢሮና የቤት መገልገያ ቁሳቁስ ስራዎች ማምረት ላይ ተሰማርቶ ውጤታማ መሆኑን ተናግሯል፡፡
በተለይ አመራሩ በሰጠን ትኩረትና በተደረገልን ድጋፍ ወደ ታዳጊና መካከለኛ ባለሃብትነት አድገን ለሌሎችም የሥራ እድል መፍጠር ችለናል ብሏል፡፡
አሁን ላይ ካፒታሉ ከ3 ሚሊዮን ብር ማለፉን ጠቁሞ ያገኘውን አጋጣሚና ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ቀጣይ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የመሰማራት እቅድ እንዳለውም ገልጿል፡፡
መንግስት ባደረገልን ድጋፍ ከአነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ወደ ታዳጊና መካከለኛ ባለሃብትነት ማደጋችን አስደስቶናል ያለችው ደግሞ በልብስ ስፌት ዘርፍ የተሰማራችው ወጣት ተሚማ መሀመድ ናት፡፡
ሶስት ሆነው በመደራጀት ባገኙት የመስሪያና መሸጫ ቦታ ጠንክረው በመስራት ለውጤት መብቃታቸውን ጠቁማ ከ10 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ጠቅሶ የዘገበው ኢዜአ ነው።



