የሥራ ዕድል ፈጠራን ጨምሮ የኢንተርፕራይዝ ምስረታና የሰልጣኝ ቅበላ በኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓ ማከናወን ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
July 14, 2025

የሥራ ዕድል ፈጠራን ጨምሮ የኢንተርፕራይዝ ምስረታና የሰልጣኝ ቅበላ በኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓ ማከናወን ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ላለፉት አራት ተከታታይ ቀናት ከተጠሪ ተቋማት፣ ከክልልና ከተማ አስተዳደሮች የዘርፉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ሲያካሄደው የነበረው የፐብሊክ ኢንተርፕረነርሺፕ፣ የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ ተጠናቋል፡፡
በማጠቃለያ መርሃ ግብር የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ሙፈሪሃት ካሚል በቀጣይ በዘርፉ ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ክብርት ሚኒስትር በማብራሪያቸው እንደገለጹት ላለፉት አራት ቀናት የተሰጠው ጊዜውን የዋጀ የአመራር ክህሎት ላይ ያተኮረ ስልጠና ዋነኛ አላማው አመራሩ ተለዋዋጭ የሆነውን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ፣ ከተለመደው ወጣ ያለና የመጪውን ጊዜ ከግምት ያስገባ እቅድ አቅዶ መተግበር እንዲችል ተጨመማሪ አቅም የሚፈጥር ነው፡፡
መንግስት ዘርፉ የሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ እና ዜጎችን ከድህነት ለማላቀቅ ያለውን ፋይዳ ተገንዝቦ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የጠቆሙት ክብርት ሚኒስትር ይህንን ግዙፍ ተልዕኮ መሸከም የሚችል ተቋም መገንባት ከእያንዳንዱ አመራር ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በቴክኒክና ሙያ የሚሰጡ አጫጭርና መደበኛ ስልጠናዎች ከሰዎች መክሊት ጋር የተሳሰሩ ማድረግ፣ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ማስ ፕሮዳክሽን ማሸጋገር፣ የቴክኒክና ሙያ ኢንዱስትሪ ትስስር ማጠናከር፣ ድጅታል የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ግንባታ፣ በዘርፉ የሚሰጡ ስልጠናዎች እና የሰልጣኝ ቅበላ ስራዎች በኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት እንዲከናወኑ ማድረግ የመሳሰሉ ስራዎች በዋናነት ከቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ እንደሚጠበቁ ገልጸዋል፡፡
ጥራት ያለው እና ዘላቂ የሥራ እድል ለመፍጠር የተጀመረውን የቤተሰብ እና የማህበረሰብ ቢዝነስ ማጠናከር፣ የገጠር ትራንስፎርሜሽን የሚያረጋግጡ የግብርና እሴት ሰንሰለቶች የሚፈጥሩት የሥራ ዕድል አሟጦ መጠቀም፣ የሥራ ማዕከላትን ማጠናከር፣ የኢንተርፕራይዝ ምስረታ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ በኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት አማካይነት ማከናወን ልዩ ርብርብ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡
ከአሠሪና ሰራተኛ ዘርፍ አኳያም በውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት ዘርፍ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ የህግ ማዕቀፍ ሪፎርም መደረጉን ገልጸው የኤጀንሲዎች ሪፎርምም መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ የዚህ ሪፎርም ዋና አላማም ዜጎችን ከህገ ወጦች መከላከል፣ ክብርና ደህንነታቸውን ማረጋገጥ እና ሀገርም ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር የጸደቀው የህግ ማዕቀፍ ከቤት ውስጥ ረዳቶች ባሻገር የሰለጠኑና በከፊል የሰለጠኑ ዜጎች ወደ መዳረሻ ሀገራት መላክ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በ2018 በጀት ዓመት የሥራ ባህል ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት፣ የምርታማነት ምክክር ማጠናከር፣ የኢንዱስትሪ ሰላም ማረጋገጥ እና የሚገጥሙ ችግሮች በአዲሱ ትርክት ከክርክር ይልቅ በምክክር መፍታት አጽንኦት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡












