ግብርናን በማዘመን በዘርፉ እየታየ ያለውን ውጤት ለማላቅ የባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
September 23, 2024
ግብርናን በማዘመን በዘርፉ እየታየ ያለውን ውጤት ለማላቅ የባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
ሁሉንም የግብርና ልማት ጣቢያ ባለሙያዎችን ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችል መርሃ ግብር በቅርቡ እንደሚጀምር ተጠቆመ
መርሃ ግብሩ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት ተግባራዊ የሚያደርጉት ነው፡፡
ይህን በተመለከተ የተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶችና አስፈላጊነቱ ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል እና የግብርና ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ግርማ አመንቴን ጨምሮ የክልል ግብርና ቢሮ፣ የግብርና ኮሌጆች እንዲሁም የሁለቱም ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ ግብርናን በማዘመን በዘርፉ እየታየ ያለውን ውጤት ለማላቅ የባለሙያዎች አቅም ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡
ተግባራዊ የሚደረገው የግብርና ልማት ጣቢያ ባለሙያዎች የደረጃ ማሻሻያ ግብርና ሚኒስቴር የጀመረውን ውጤታማ ሥራ የሚያጠናክርና እየተገኘ ያለውን ውጤት በእጅጉ ከፍ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
በአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ የቴክኒክና ሙያ ስርዓቱ እስከ ደረጃ 8 ድረስ እንዲዘልቅ መደረጉን ጠቁመው በዘርፉ ሥራ ፈላጊ ብቻ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ ዜጎችን ማፍራት የሚያስችል የሙያ ደረጃና ሥርዓተ ትምህርት መዘጋጀቱን አመላክተዋል፡፡
በቀጣይ ከግብርና ማሰልጠኛ ኮሌጆች ሰልጥነው የሚወጡ ዜጎች ዘርፉን ከማዘመንና ምርትና ምርታማነት እንዲረጋገጥ ከሚያደርጉት ሙያዊ ድጋፍ ባለፈ በሙያቸው ኩባንያ እንዲመሰርቱ የሚፈለግ መሆኑን የጠቆሙት ክብርት ሚኒስትር ለዚህም አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ላለው ውጤት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉት የልማት ጣቢያ ባለሙያዎች ናቸው፡፡
ደረጃቸውን ለማሻሻል ያለመው ይህ መርሃ ግብር በዘርፉ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ከማሳደግ ባለፈ ተነሳሽነታቸውን እንዲጨምር የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
የግብርና ልማት ጣቢያ ባለሙያዎችን ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችለው መርሃ ግብር በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግም ነው ክቡር ሚኒስትሩ የጠቆሙት።