Mols.gov.et

የዘርፍን ውጤታማነት የማላቅ ግብ ያለው ቴክኒካዊ ድጋፍና ክትትል

March 19, 2026
የዘርፍን ውጤታማነት የማላቅ ግብ ያለው ቴክኒካዊ ድጋፍና ክትትል የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በዘርፉ የታቀዱ የለውጥ አጀንዳዎችና ስትራቴጂካዊ ግቦች ውጤታማ መሆናቸውን ለማረጋገጥ፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች የሚከናወን መጠነ-ሰፊ የቴክኒክ ድጋፍና የመስክ ክትትል ሥራ ጀምሯል። የክትትልና ድጋፍ ሥራውን የሚመሩት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ነቢሃ መሐመድ እንደገለጹት፤ ይህ የመስክ ምልከታ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሀገራዊ ተልዕኮውን በስኬታማነት ለማስፈፀም የቀረፃቸውን እሳቤዎችን ተግባራዊነት ለመመዘን የሚያስችል ነው፡፡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት በከፍተኛ አመራሮች የተመራ የክትትልና ድጋፍ ቡድን በ10 ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ምልከታ ማድረጉን ያስታወሱት ክብርት ነቢሃ የታዩ ክፍተቶችን መሠረት በማድረግ ለክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና ለዘርፍ ቢሮ ኃላፊዎች በተሰጠው ግብረ-መልስ መሰረት ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ዕቅዳቸውን ከልሰው ወደ ተግባር መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡ ቴክኒካል ባለሙያዎችን ያካተተው የአሁኑ የመስክ ምልከታ ዋና ዓላማ በአመራር ደረጃ በቸካሄደው የድጋፍና ክትትል ሥራ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የገቡትን ቁርጠኝነትና የጀመሩትን የሥራ አፈጻጸም በተጠናከረ መልኩ እንዲፈጽሙ የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት መሆኑም ተመላክቷል፡፡ ይህ የሱፐርቪዥን ቡድን በየክልሎቹ ከሚገኙ አቻ የቴክኒክ ቡድኖች ጋር በቅንጅት በመሥራት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በክህሎት ልማትና በኢንዱስትሪ ሰላም ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችን በቦታው በመገኘት የሚፈታና የልምድ ልውውጥ የሚያደርግ ይሆናል። በመሆኑም በየደረጃው የሚመለከታቸው አካላት ለክትትልና ድጋፍ ቡድኑ አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ፣ የዘርፉን ሥራዎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ ክብርት ነቢሃ ጥሪ አቅርበዋል።
en_USEN
Scroll to Top