Mols.gov.et

የዓለም የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋማት ማህበር አባል መሆን የቻለው ኢኒስቲትዩት

July 18, 2024
የዓለም የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋማት ማህበር አባል መሆን የቻለው ኢኒስቲትዩት የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ በማዘጋጀትና ከዘርፉ ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር የስራ ትስስር በመፍጠርና ቅንጅታዊ አሰራርን በማሳደግ በበጀት ዓመቱ በርካታ ስራዎችን ማከናወኑ ተገለፀ፡፡ የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት 160 ከሚሆኑ ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ባለድርሻ አካላት ጋር የሥራ ትስስር በመፍጠር በበጀት አመቱ ውጤታማ ስራዎችን መስራት ችሏል፡፡ በመደበኛ መርሃ-ግብር በደረጃ እና በዲግሪ ፐሮግራም ስልጠና መስጠት የሚያስችሉ 4 ኮርስ ካታሎግ ሲዘጋጅ ከዚህ ዉስጥ በቱሪዝም ማኔጅሜንት እና በሆቴል ማኔጅሜንት በዲግሪ መርሃ-ግብር በራስ አቅም ስልጠና ለመጀመር የስርዓተ-ትምህርት ክለሳ አድርጓል፡፡ የISO-21001:2018 የጥራት ሥራ አመራርን የተቋሙ አሰራር ማዕቀፍ አድርጎ በመዘርጋት ከሚመለከተዉ አካል እዉቅና ያገኘ ሲሆን ቴክኒካል ኮሚቴ እና አስፈጻሚ ግብረ-ሀይል በማቋቋም በተሰራው ስራ አፈጻጸሙን 86% ማድረስ ችሏል፡፡ የተቋሙ አሰልጣኞችና ሰልጣኞች በምግብና መጠጥ ዝግጅት፣ በቤት አያያዝ፣ በጉብኝት ሥራ እና በምግብና መጠጥ መስተንግዶ ላይ ትኩረት በማድረግ 11ኛዉ የክህሎትና የመስተንግዶ ሳምንት በድምቀት አካሂዷል፡፡ ተመራቂ ሰልጣኞችን ከአሰሪዎች ጋር ለማገናኘት አሰሪና ሰራተኛ የሚያገናኝ ጆብፌር ተዘጋጅቶ 40 የሚሆኑ የዘርፉ ተቋማት በመገኘታቸዉ ለምሩቃኑ የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡ ለባህላዊ ምግብ ዝግጅት ልዩ ትኩረት በመስጠት በተለያዩ አካባቢዎች ከአስተዳደር አካላት እና ከልዩ ልዩ ብሄረሰብ አባላት ጋር በመቀናጀት የባህላዊ ምግቦች ተለይተዉ የምግብ አዘጋጃጀት ሰነድ የመቀመር ስራ ተሰርቷል፡፡ ባህላዊ ምግቦችን ወደ ኢንደስትሪዉ ለማሸጋገር ከባለ ኮከብ ሆቴሎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ዉይይት በማድረግና የባህላዊ ምግብ ፌስቲቫል በማዘጋጀት ሆቴሎች አማራጭ የምግብ ሜኑ አድርገዉ እንዲጠቀሙበት እና በዚህ ዙሪያ ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር በሚቻልበት አግባብ ላይ ሰፊ ግንዛቤ የማስረጽ ስራ ተሰርቷል፡፡ የማሰልጠኛ ተቋሙ ቀደም ብሎ ከዓለም ቱሪዝም ድርጅት፣ ከዓለም ባንክ እና ከጀርመን ልማት ባንክ ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በበጀት ዓመቱ ደግሞ 175 አባላት ካሉት የዓለም የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋማት ማህበር አባል መሆን ችሏል፡፡ በመሆኑም ከነዚህ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የመሰረተዉን ግንኙነት የስልጠና እና የምርምር አቅሙን ለማሳደግ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በምስራቅ አፍሪካ የቱሪዝምና እንግዳ ተቀባይነት ልህቀት ማዕከል የመሆን ርዕዩን ለማሳካት እየተጋ ይገኛል፡፡
en_USEN
Scroll to Top