የኢንዱስትሪ ማህበረሰብ ምክክርን በመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ለማስጀመር የሚያስችል የአስተባባሪዎች ስልጠና ተሰጠ፡፡
የአሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ በስልጠናው መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነትን ለማጠናከር ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ምክክሮችን ማካሄድ አንዱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ምክክር በኢንዱስትሪዎች ውስጥ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያግዝ ዋነኛ ስልት እየሆነ መምጣቱን የጠቆሙት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ምቹ የሥራ አካባቢን ከማረጋገጥ አንስቶ ምርታማነትን በማሳደግ በሀገር ቀጣይ እድገት ላይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል አዲስ እሳቤ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ የኢንዱስትሪ ማኀበረሰብ የምርታማነት ምክክር የሚመረበት ማንዋል በማዘጋጀት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፣በኦሮሚያ እና በሲዳማ ክልሎች በተመረጡ ተቋማት ለአመቻቾችና አስተባባሪዎች ስልጠና መስጠቱ በመድረኩ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር አዲስ እሳቤን እና የኢንዱስትሪ ማህበረሰብ ምክክር የሚመራበት ማስፈፀሚያ ማኑዋልን የተመለከቱ ገለፃዎች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡