የኢንዱስትሪውን ፍላጎት ለማሟላት የግብርና ኮሌጅ
August 12, 2026
የኢንዱስትሪውን ፍላጎት ለማሟላት የግብርና ኮሌጅ አመራሮች የፕሮጀክት አስተዳደር አቅም መጠናከር
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከSNV ኢትዮጵያ የሆርቲ-ላይፍ (Horti-LIFE Green Growth) ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በሆርቲካልቸር ልማትና በክህሎት ማሳደግ ላይ ያተኮረ የስድስት ወር አፈፃፀም ግምገማ፣ ውይይትና የሥልጠና መርሃ-ግብር በአዲስ አበባ አካሄደ።
በመድረኩ ላይ ከሰባት ክልሎች የተወጣጡ የ60 የግብርና ቴክኒክና ሙያ (A-TVET) ኮሌጆች ዲኖች፣ ምክትል ዲኖች፣ የመንግሥት አካላትና አጋሮች ተሳትፈዋል።
የመርሃ-ግብሩ ዋና ዓላማ የ15ቱን ኮሌጆች የሥራ አፈጻጸም፣ ምርጥ ተሞክሮዎች፣ የተማሪዎች የልምምድ ማሳ እና የአርሶ አደሮች የመስክ ስልጠና እንቅስቃሴዎችን በጋራ መገምገም እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም የአመራሩን የፕሮጀክት አስተዳደር አቅም በማጠናከር ተወዳዳሪና የኢንዱስትሪውን ፍላጎት የሚያሟላ የሰው ኃይል ለማፍራት መድረኩ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡
በሁለት ምዕራፍ በተካሄደው በዚህ ፕሮግራም በመጀመሪያው ቀን፤ በኮሌጆች የተከናወኑ የሥራ አፈጻጸሞችና የመልካም ተሞክሮ ልውውጦች የተካሄዱ ሲሆን፣ በቀጣዮቹ ሶስት ቀናት ደግሞ በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባላቸው ባለሙያዎች አማካኝነት ለኮሌጅ አመራሮች የፕሮጀክት ቀረጻ፣ የሀብት፣ የጊዜና የአደጋ አስተዳደር እንዲሁም የክትትልና ግምገማ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።
በመጨረሻም የኮሌጆቹን የ2018/19 ዓ.ም የጋራ የሥራ እቅድ በማጽደቅና ለሰልጣኝ አመራሮች የስልጠና ማጠናቀቂያ ሰርተፊኬት በመስጠት መርሃ-ግብሩ ተጠናቋል።









