የኢንተርፕራይዞች ምርታማነት ለሀገር ብልጽግና…
April 2, 2026
“የኢንተርፕራይዞች ምርታማነት ለሀገር ብልጽግና”፦ ታላቁ አውደ ርዕይ በመስቀል አደባባይ በደመቀ ሁኔታ ተከፈተ!
የመዲናችን የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆኑት ኢንተርፕራይዞች የሥራ ውጤታቸውን ይዘው አደባባይ ወጥተዋል! በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ አዘጋጅነት የሚካሄደውና ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆየው ዓመታዊ የኢንተርፕራይዞች ሳምንት አውደ ርዕይና ባዛር በመስቀል አደባባይ በደመቀ ሁኔታ ተከፍቷል።
የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በመክፈቻው ላይ እንደገለጹት፣ መንግስት የሰው ኃይልን ወደ ምርታማነት ለመቀየር ባደረገው ጥረት ባለፉት ዓመታት ብቻ ከ2 ሚሊዮን በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ በበኩላቸው፣ ዘርፉ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋትና ለኢንዱስትሪ ሽግግር ያለውን ፋይዳ አብራርተዋል። ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ ብቻ ለ11,605 ኢንተርፕራይዞች ከ13.5 ቢሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፈጠሩንም አስታውቀዋል፡፡
በተመሳሳይ ለ5,983 አንቀሳቃሾች 2.8 ቢሊዮን ብር ብድር የቀረበ ሲሆን፣ ለ1,571 ኢንተርፕራይዞች የ706.3 ሚሊዮን ብር የመሣሪያ ሊዝ ድጋፍ ተደርጓል። 10,921 ኢንተርፕራይዞች ደግሞ ከጥቃቅን ወደ አነስተኛ ደረጃ መሸጋገራቸው በመድረኩ ተገልጿል፡፡







