Mols.gov.et

የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ከስራ ፈጠራ ባሻገር…

July 23, 2024
የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ከስራ ፈጠራ ባሻገር ለአገልግሎት ዘርፍ ኢንቨስትመንት መጎልበት ሚናው የጎላ ነው የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ከስራ ፈጠራ ባሻገር ለአገልግሎት ዘርፍ ኢንቨስትመንት መጎልበት ሚናው የጎላ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአምስት ሚሊየን ኮደርስ ኢኒሼቲቭን በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል፡፡ ኢኒሼቲቩ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስና የኢትዮጵያ መንግስታት የሚተገበር ሲሆን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ 5 ሚሊዮን ወጣቶች በኦንላይን የኮዲንግ ስልጠና የሚወስዱበት ነው፡፡ ስልጠናውም በዋናነት በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ ከኢኒሼቲቩ ማስጀመሪያው በተጓዳኝ የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ላይ ትኩረት ያደረገ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ ከተሳተፉት መካከል የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ ኢኒሼቲቩ የትምህርት ዘርፉ ብቁ ትውልድ ለመገንባት በሚያከናውነው ስራ ላይ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው አብራርተዋል፡፡ በተለይ ትውልዱ በንድፈ ሃሳብ የሚያገኛቸውን እውቀቶች በቀላሉ ወደ ተግባር እንዲለውጥ ምቹ እድል በመፍጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል ነው ያሉት፡፡ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው ቴክኖሎጂ ከስራ ፈጠራ ጋር የሚተሳሰር ዘርፍ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የወጣቶችን ዲጂታል አቅም ለመገንባት የተሰጠው ትኩረት ደግሞ ግብርናን ጨምሮ የተለያዩ መስኮችን ለማዘመን የተያዘውን ውጥን እውን ለማድረግ እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት፡፡ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግስትን ወክለው በፓናሉ የተሳተፉት አብዱልአዚዝ አልጃዝሪ በኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂን እውን በማደረግ ረገድ ከፍተኛ የሆነ የአመራር ቁርጠኝነት መኖሩን አንደታዘቡ ተናግረዋል፡፡ ይህ ደግሞ በኢኒሼቲቩ የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ ቴክኖሎጂ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ በእጅጉ እየቀየረ ስለመሆኑ አንስተው፤ ከዚህ አኳያ ለዘርፉ ቅድሚያ መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡ የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ከ10 ዓመቱ መሪ የልማት አቅድ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ያብራሩት ደግሞ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ በእቅዱ ላይ ዲጂታል ክህሎትን መሰረት ያደረገ የሰው ኃይል ልማት ትኩረት እንደተሰጠው ጠቅሰው፤ ኢኒሼቲቩም ይህን እውን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ኢኒሼቲቩ በኢትዮጵያ ክህሎት ያለው የሰው ሃይልን በመገንባት ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በአገልግሎቱ ዘርፍ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡ የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ዘመናዊና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥን እውን ማድረግ መንግስት እያከናወነ ያለው የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ አካል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግስት ሰራተኞች ዲጂታል ክህሎት ማደግ እንዳለበት ጠቅሰው፤ ኢኒሼቲቩም የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያውን የሚያግዝ እንደሆነ ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
en_USEN
Scroll to Top