የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት አዲስ ተስፋ ይዞ እንደሚመጣ የሚጠበቀው ስምምነት
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋም የሆነው የፌዴራል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ ያለውን አቅም ለማጠናከር እና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችለውን የጋራ የትብብር ስምምነት ተፈራርሟል።
ይህ ስምምነት በትምህርት ላይ ብቻ ሳይወሰን በሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኙ የበለጸጉ የቱሪስት መስህቦችን በተለይም የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን የቱሪዝም ሀብቶች በዘላቂነት ለማልማትና ለማስተዋወቅ የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት በቴክኒክና በዕውቀት ለመደገፍ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል።
የፌዴራል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አመራሮችና ባለሙያዎች ለስምምነቱ መሳካት ላሳዩት ቁርጠኝነት የዩኒቨርሲቲው አመራር ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፣ ይህ አጋርነት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በዕውቀትና በክህሎት የሚመራ ብቁ የሰው ኃይል ለመገንባት በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ስምምነት ተቋማቱ ያላቸውን አቅም በማቀናጀት ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት አዲስ ተስፋ ይዞ እንደሚመጣም ይጠበቃል።