የሲዳማ ክልል የሥራና ክህሎት ቢሮ የሪፎርም ትግበራውን ወደ ተግባር አሸጋገረ
በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የቴክኖሎጂና የሥራ ባሕል ዕድገትን የሚመጥን ዘመናዊ የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችለው የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ወደ ተግባር ምዕራፍ መሸጋገሩ ተገለጠ።
ይህንንም ተከትሎ ቢሮው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ለአመራሮች፣ ለዓብይና ለቴክኒካል ኮሚቴ አባላት ለሁለት ቀናት የሚቆይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት ላይ ነው።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር አማካሪ አቶ አዝመራ ከበደ የሪፎርም ሥራዎችን በአግባቡ መተግበር ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎትን በማቅረብ ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።
ሪፎርሙ በሰው ሀብት ልማት ላይ ትኩረት የሚያደርግ መሆኑን የጠቀሱት አማካሪው፣ የተገልጋይን እርካታ ለማረጋገጥ የበቃና ዝግጁ የሆነ የሰው ኃይል መፍጠር እንደሚገባም አስረድተዋል።