የሥራ ቦታዎች ምቹ መሆን ለምርታማነትና ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ
May 14, 2026
የሥራ ቦታዎች ምቹ መሆን ለምርታማነትና ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ
በኢትዮጵያ የቡና እና የሆርቲካልቸር የዕሴት ሰንሰለቶች ውስጥ ምቹ የሥራ ሁኔታን (Decent Work) ለማረጋገጥና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የተዘጋጀው ሀገራዊ የፕሮጀክት ዓብይ ኮሚቴ የመጀመሪያ ስብሰባውን በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የሥራ ቦታዎች ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ ምርትና ምርታማነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትንና ተገቢውን የገበያ ድርሻ ለማግኘት ያስችላል ሲሉ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ቡና እና ሆርቲካልቸር የዕሴት ሰንሰለቶች ምቹ የሥራ ሁኔታን ማሻሻል ፕሮጀክት በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና በዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት (ILO) አማካኝነት በኦሮሚያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያና ከሲዳማ ክልሎች ይተገበራል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ምቹ የሥራ ሁኔታን (Decent Work) በሀገሪቱ ለማረጋገጥ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ቀርፆ እየተገበረ ይገኛል።
ይህም በአዲሱ የሪፎርም አስተሳሰብ የሥራ ቦታዎች ሰላምን በማረጋገጥ፣ የሠራተኞችን ደህንነትና ጤንነት በመጠበቅ ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ የሚያጠናክር ነው።
በመድረኩ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን ጨምሮ የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መ/ቤቶችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ትግበራ ላይ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ፣ በአሰሪዎች፣ በሠራተኞች እና በአጋር ድርጅቶች መካከል የሚፈጠረው ቅንጅት ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ የሥራ ሁኔታ ምቹነት እንዲረጋገጥ፣ በሥርዓተ-ጾታ እኩልነት እና በሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ዙሪያ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት እንዲፈቱ እንደሚያግዝ ተገልጿል።
በመንግሥትና በማህበራዊ አጋሮች መካከል የሚፈጠር ጠንካራ ቅንጅት የግብርና ምርት ምሰሶ የሆነውን የቡና እና የአትክልት ምርቶቻችን ያለችግር ኤክስፖርት ለማድረግ የሚያስችል የ(Labor Compliance) ተፈፃሚነት በማሳደግ፣ የተሻለ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ዘላቂ የሆነ አገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ቁልፍ መሣሪያ መሆኑ ተመላክቷል።




