የሙያ ብቃት ምዘናና ሰርተፊኬሽን ስርዓቱ: አዲስ ምዕራፍ
November 7, 2025
የሙያ ብቃት ምዘናና ሰርተፊኬሽን ስርዓቱ: አዲስ ምዕራፍ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሙያ ብቃት ምዘናና ሰርተፊኬሽን ስርዓቱ የስልጠና አግባብነትንና ጥራትን በሚጠበቀው ልክ የሚያሻሽልና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ለማድረግ መሰረተ ሰፊ ሪፎርም እያካሄደ ይገኛል።
የሪፎርሙ ዋነኛ ትኩረት ተዓማኒ፣ ግልፅ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ፣ በቴክኖሎጂ የሚታገዝ እና የኢንዱስትሪውን ባለቤትነት ያረጋገጠ ሀገራዊ የብቃት ምዘናና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ስርዓት በመዘርጋት ብቁ፣ ተወዳዳሪና አምራች ዜጎችን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ማላቅ ነው።
በዚህም የሙያ ብቃት ምዘናና ሰርተፊኬሽን ስርዓቱን አውቶሜት ለማድረግ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራው ተጠናቆ የትግበራ ሥራን ለማስጀመር በኦሮሚያ እና በሀረሪ ክልሎች የመጀመሪያ የአውቶሜሽን ሲስተም ስልጠና ተሰጥቷል። በቀጣይ በሁሉም ክልሎች የአውቶሜሽን ስርዓቱን ለመተግበር ከኢትዩጵያ ሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት ኘሮጀክት ጽ/ቤት ጋር በጋራ የማብቃት ሥራ የምናከናውን ይሆናል።
እንዲሁም ሁሉንም የክልልና የሁለቱም ከተማ አስተዳድሮች የሙያ ብቃት ምዘና ኤጀንሲዎች ዓለም አቀፉን ISO 17024 እውቅና እንዲያገኙ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር የቃል ኪዳን ውል የተፈራረሙ ሲሆን፣ ሲዳማ፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ወደ ተግባር ሥራ የገቡ ክልሎች ናቸው።
በተጨማሪም የአዳዲስ የምዘና መሳሪያዎችን ዝግጅት እና የብቃት ምዘና መሳሪያዎች ብዝኃነትን ለማረጋገጥ ከክልሎች ጋር በመተባበር ቢያንስ አንድ ሙያ ከ4 በላይ ተጨማሪ ቨርዥን እንዲኖረው የማድረግ ሥራም እየተከናወነ እንደሆነ የሙያ ደረጃና ሥርዓተ ሥልጠና ዝግጅትና ብቃት ምዘና መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ማርታ ወልዴ ገልጸዋል።

