Mols.gov.et

የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ፕላትፎርም ኢኮኖሚ የሥራ ደረጃ ፀደቀ

June 17, 2026
የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ፕላትፎርም ኢኮኖሚ የሥራ ደረጃ ፀደቀ የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት (ILO) 114ኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ በጄኔቫ ሲጠናቀቅ፣ በዲጂታል ዘመን የሥራ ገበያን የሚመራ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የፕላትፎርም ኢኮኖሚ የሥራ ደረጃ (Convention) በሰፊ ድምፅ በማፅደቅ ታሪካዊ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ይህ አዲስ ኮንቬንሽን በዲጂታል ፕላትፎርሞች ላይ የሚመሠረት ሥራ (platform work) ላይ የሚሰሩ ሰራተኞች የሥራ መብት፣ የሥራ ደህንነት፣ የፍትሃዊ ክፍያ እና የማህበራዊ ጥበቃ መርሆዎችን ለማጠናከር ዓለም አቀፍ መሠረት ይጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ የሚመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ንቁ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ ልዑካኑ በአሠሪዎችና በሠራተኞች ኮንፌዴሬሽኖች ጋር በጋራ በመሆን በተለያዩ ኮሚቴዎች ውይይቶች ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ በውይይቶቹ የተነሱት ዋና ጉዳዮች መካከል የዲጂታል እና ፕላትፎርም ኢኮኖሚ ሽግግር፣ የሴቶች እኩል ተሳትፎ እና ጥቅም ማረጋገጥ፣ እንዲሁም ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነትን በማጠናከር ምርታማነትን ማሳደግ ይገኙበታል፡፡ አዲሱ የተፀደቀው ዓለም አቀፍ የሥራ ደረጃ በተለይ በፈጣን የዲጂታል ዘመን ላይ የሚሰሩ ሠራተኞች በግልፅ የሥራ መብት እና የጥበቃ ስርዓት እንዲያገኙ የሚያስችል የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ማዕቀፍ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በሌላ በኩል በዲጂታል እና በአረንጓዴ የልማት ሽግግሮች ወቅት ሴቶች እኩል የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ሥርዓታዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ በመንግስታት፣ በአሠሪዎች እና በሠራተኞች መካከል ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ስታንዳርዶችን ማሻሻል ሌላው የተወያዩበት ዋና ነጥብ ነበር፡፡
en_USEN
Scroll to Top