Mols.gov.et

የሉባን ስልጠና ማዕከል በክህሎት ልማቱ ዘርፍ …

March 22, 2024
“የሉባን ስልጠና ማዕከል በክህሎት ልማቱ ዘርፍ ጊዜውን በዋጀ ቴክኖሎጂ ስልጠና እንድንሰጥ ከማስቻሉ ባሻገር የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂያዊ አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው፡፡” ክቡር ዶ/ር ተሻለ በሬቻ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ በኢትዮጵያ የክህሎት ልማት ዘርፍ በተለያየ መልኩ በመደገፍ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ሀገራት መካከል ቻይና አንዷ ናት፡፡ ቻይና የቀድሞ ኢትዮ-ቻይና ኮሌጅ በመባል የሚታወቀውን የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ገንብቶ በቁሳቁስ ከማሟላት አንስቶ በትምህርትና ሥልጠናው ዘርፍ የተለያዩ ድጋፎችን ስታደርግ ቆይታለች፡፡ አሁንም በተለያየ አግባብ ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች፡፡ እ.አ.አ 2021 ከቻይናው ቲያንጂን የቴክኖሎጂ እና ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ትብብር በኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የሉባን ስልጠና ማዕከል ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል፡፡ ስልጠና ማዕከሉ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ውስጥ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ሮቦቲክስን ጨምሮ በሴንሰር ቴክኖሎጂ፣ በሜካትሮኒክስ እና በኢንዱስትሪ ቁጥጥር የሙያ መስኮች ስልጠና መስጠት የሚያስችል ነው፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል እያደገ የመጣውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር በቻይና ትምህርት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዋና ዳይሬክተር ሊ ዪንግሊ የተመራ የልዑካን ቡድን በኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የሚገኘውን ሉባን ስልጠና ማዕከል ጎብኝቷል፡፡ የልዑካን ቡድኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ተሻለ በሬቻን ጨምሮ የኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ አመራሮች ተቀብለዋቸዋል፡፡ የልዑካን ቡድኑ መሪ ሊ ዪንግሊ ከጉብኝቱ በኋላ እንደገለጹት፣ በትምህርትና ስልጠናው ዘርፍ ቻይና የኢትዮጵያን የልማት ግቦች ሊያሳኩ የሚችሉ ድጋፍ ማድረጓን ትቀጥላለች፡፡ ቻይና በኢትዮጵያ ያቋቋመችው የሉባን ስልጠና ማዕከል ከኢትዮጵያ ባለፈ ለቃጣናው እና ለአፍሪካውያንም ጭምር ፋይዳው ትልቅ ነው፡፡ በቅርቡም በባቡር ቴክኖሎጂ ላይ የሚያተኩር በኢትዮጵያ ሁለተኛውን የሉባን የስልጠና ማዕከል ይቋቋማል ብለዋል፡፡ ለተግባራዊነቱም የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ም/ል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ሀፍቶም ገ/እግዚሀብሔር እና የቻይና ትምህርት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዋና ዳይሬክተር ሊ ዪንግሊ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ፈርመዋል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ተሻለ በበኩላቸው፤ ቻይና እያደረገች ለሚገኘው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው የሉባን ስልጠና ማዕከል በክህሎት ልማቱ ዘርፍ ጊዜውን በዋጀ ቴክኖሎጂ ስልጠና እንድንሰጥ ከማስቻሉ ባሻገር የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂያዊ አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው ብለዋል፡፡
Scroll to Top

The Ministry of Labor & Skills