ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን በማጠናከር..
June 23, 2026
ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን በማጠናከር የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን በማጠናከር የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለጹ፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በለውጡ መንግሥት የተተገበሩ የሪፎርም ሥራዎች የወጣቶችን ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተጨባጭ ውጤቶችን አስገኝተዋል።
ባለፉት 4 ዓመታት በተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ የሪፎርም ሥራዎች ለ19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠራቸውን ጠቁመው፣ ከዚህም መካከል 75 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወጣቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለውጡ ካስገኛቸው ዋና ዋና ስኬቶች መካከል ወጣቶች ከተለመደው የቅጥር ሐሳብ ወጥተው ወደ ሥራ ፈጣሪነት እንዲሸጋገሩና ለሌሎች የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ምቹ ሁኔታዎችን መፈጠራቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም የቤተሰብ የንግድ ሥራዎች እንዲስፋፉ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን አክለዋል፡፡
የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች መስፋፋትና ለዘርፉ የተሰጠው ልዩ ትኩረት ለወጣቶች ዘመናዊ፣ ፈጣንና ምቹ የሥራ ዕድሎችን የፈጠረ ሲሆን፣ ይህም በዓለም አቀፍና በአህጉራዊ የዲጂታል የሥራ ገበያ ላይ የሀገሪቱንና የወጣቶቹን ተወዳዳሪነት ማሳደጉን አብራርተዋል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አሕመድ በበኩላቸው፤ ከለውጡ በኋላ የወጣቶችን አቅም በማሳደግ ረገድ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም ተስፋ ሰጪ፣ ዘላቂና ክህሎት መር የሥራ ዕድሎችን በተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር ትልቅ አቅም መገንባቱን አብራርተዋል።
በመዲናዋ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወጣት ጋሻው ዓለሙ የመኪና ጎማና ባትሪዎችን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ሥራ ላይ መሰማራቱን ጠቅሷል፡፡
የምናመርታቸው ምርቶች የአካባቢ ብክለትን ከመቀነስና ቆሻሻን ወደ ሀብት ከመቀየር ባለፈ፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን የሚያሳድጉና ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው ብሏል።
በማኅበር በመደራጀት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ የቤትና የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶችን እያመረቱ መሆናቸውን የተናገረው ደግሞ ወጣት አስቻለው ጌትዬ ነው፡፡
በቀጣይም የምርቶቻቸውን የገበያ ተደራሽነትና የሥራ ዕድሎችን ይበልጥ ለማስፋፋት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግሯል። መረጃው የኢዜአ ነው።





