ከ26 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረው የከተማ ግብርና
በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት 8 ወራት ብቻ በከተማ ግብርና ዘርፍ ከ 26 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የሥራ ስምሪት አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰብሃዲን ሱልጣን እንደገለጹት፤ 2,088 አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም በቅጥር ከ 26 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ ባለፉት 8 ወራት ከተፈጠረው 287 ሺህ በላይ ቋሚ የሥራ ዕድል ውስጥ የከተማ ግብርና የ 9.3 በመቶ ድርሻን ይዟል።
በከተማዋ የሥራ ዕድል ሊፈጠርባቸው የሚችሉ 44,307 የከተማ ግብርና ጸጋዎች ተለይተው ወደ ሥራ መገባቱን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ ኢንተርፕራይዝ በማደራጀት ብቻ 17,404 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡
የከተማ ግብርና ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር የተሻገረ ፋይዳ እንዳለው የጠቆሙ ዳይሬክተሩ ለነዋሪዎች የዕለት ተዕለት የምግብ ፍጆታ የሚውሉ (አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ዶሮና እንቁላል…) የመሳሰሉ ምግቦች በራስ ግቢና አካባቢ በማምረት የኑሮ ውድነትን መቋቋም ያስችላል ብለዋል።