ከ120 ሺህ በላይ ወጣቶችን ለማብቃት ያለመው ኢኒሺየቲቭ
December 18, 2025
ከ120 ሺህ በላይ ወጣቶችን ለማብቃት ያለመው ኢኒሺየቲቭ
በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለማፋጠን እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ያስቀመጠውን የሰው ኃይል ልማት ግብ ለማሳካት፤ በአማራ ክልል በ”ዲጂታል አማራ ኢንሼቲቭ” አማካኝነት ከ120 ሺህ በላይ ወጣቶችን በዲጂታል ክህሎት ብቁ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።
ይህ መርሃ ግብር በተለይም የክልሉ የሥራና ክህሎት ቢሮ ከትምህርት ቢሮ እና ከክልሉ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ዴሊቨሪ ዩኒት ጋር በመቀናጀት “ዲጂታል ክህሎት ለሥራ ፈጠራ እና ሙያ ልማት” በሚል መሪ ቃል በኮምቦልቻ ከተማ የአሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት ላይ ነው።
የክልሉ የሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አማረ ዓለሙ እንደገለጹት፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በቴክኖሎጂ በማገዝ ወጣቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በመሠራት ላይ ነው።
በዚህም ወጣቶች በዲጂታል ማርኬቲንግ፣ በኔትወርክ ኮንፊግሬሽን፣ በግራፊክ ዲዛይን፣ በዌብ ዲቨሎፕመንት እና በኮንቴንት ክሬሽን ዘርፎች የላቀ እውቀት እንዲጨብጡ በማድረግ የሀገር ግንባታ ሚናቸውን እንዲወጡ ታቅዷል።
ይህ ሥራ የሀገሪቱን ብልጽግና በአጭር ጊዜ ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ የተቀናጀ የወጣቶች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆኑን አመልክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም፣ የትምህርት ጥራትና የክህሎት ሽግግርን ለማፋጠን ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ የትምህርት ስርዓቱ በዲጂታል አሠራር እንዲቃኝ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል። በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የICT ዳይሬክቶሬት እና በዘርፉ ባለሙያዎች የተደገፈው ይህ ንቅናቄ፣ ወጣቶች ዘመኑን የዋጀ ክህሎት እንዲታጠቁ ከማድረግ ባለፈ፣ የኮምቦልቻ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን በምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ የክህሎት ትስስርና የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየተከናወነ ያለውን ተግባር የሚያግዝ ነው።



