Mols.gov.et

ከአሰልቺ አሠራር ወደ ቀልጣፋው የአገልግሎት ማዕከል(መሶብ)

April 1, 2026
ከአሰልቺ አሠራር ወደ ቀልጣፋው የአገልግሎት ማዕከል(መሶብ) የሥራ ባህል ለውጥ በሀገራችን ኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች ጀምሮ በመጨረስ እና የመንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት በማዘመን ሂደት እየተገለጠ ይገኛል፡፡ ከልማት ፕሮጀክቶች አኳያ በኮሪደር ልማትና በሌሎችም ግንባታዎች ላይ የምናየው የቀንና ሌሊት ትጋት፣ ሥራን የዜግነት ክብር አድርጎ የማየት ባህል እየዳበረ መምጣቱን ያሳያል። በተመሳሳይ መንግስት ዜጎችን ከእንግልት ለማዳን በመሶብ አንድ ማዕከል ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለዜጎች በማቅረብ ረገድ አርአያ የሚሆን ሥራ እያከናወነ ይገኛል። በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎታቸውን እያቀረቡ ከሚገኙ ተቋማት መካከል ደግሞ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተጠቃሽ ነው፡፡ ሚኒስቴሩ የውጭ ሀገር ዜጎች የሥራ ፈቃድ እድሳት እና ክሊራንስ የመሳሰሉ አገልግሎቶች እየሰጠ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተለያዩ የሥራና ክህሎት ቢሮ አገልግሎቶችን ወደ መሶብ አስገብተው ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽ ከተደረገባቸው ክልሎች አንዱ የሆነው የሲዳማ ክልል በማዕከሉ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች የኢንተርፕራይዝ ምዝገባ እና የሥራ ምዝገባ ይገኙበታል፡፡ በዚህም ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ መሆኑ የሲዳማ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ከፍያለው ከበደ ገልጸዋል፡፡ የሥራ ባህል ምንነት በዋናነት የሚለካው ለተገልጋይ በሚሰጥ ክብርና ለጊዜ በሚሰጥ ዋጋ ነው ያሚሉት አቶ ከፍ ያለው ቀደም ሲል አንድ ዜጋ የሥራ ምዝገባ፣ ንግድ ለመጀመር ወይም ልዩ ልዩ ፈቃዶችን ለማግኘት በየመሥሪያ ቤቱ ሲንከራተትና ሲንገላታ ይስተዋል ነበር። አሁን ግን የመሶብ አንድ ማዕከል ይህንን እንግልት በማስቀረት ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ጣራ ስር እንዲያገኙ አስችሏል ብለዋል። እንደ አቶ ከፍያለው ገለጻ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥን ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት በማድረግ አዲስ የሥራ ባህል መፍጠር አስችሏል። አገልግሎቱ ተደራሽ በሆነባቸው አካባቢዎች እንደ ኮሪደር ልማቱ ሁሉ፣ በመሶብ ማዕከላትም የሚታየው ቁርጠኝነት አገልግሎቶች በተቀመጠላቸው የሰዓት ገደብ (Service Level Agreement) እንዲጠናቀቁ ከማድረጉም በላይ የመንግሥት ሠራተኛው ለዜጎች ያለውን አገልጋይነትና ለሥራው ያለውን ታማኝነት በተግባር የሚያሳይበት መድረክ ሆኗል። አንድ ፕሮጀክት በወቅቱ ሲጠናቀቅ ሀገር እንደምታተርፈው ሁሉ፣ አንድ ዜጋ አገልግሎትን ያለ እንግልት ሲያገኝም ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። እንግልት ሲቀንስ ዜጋው ጊዜውንና ጉልበቱን ምርታማነት ላይ ያውላል። መሶብ አንድ ማዕከል ይህንን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር፣ ዜጎች በሀገራቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑና በኢኮኖሚው ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረጉን ቀጥሏል።
en_USEN
Scroll to Top