እንተርፕራይዞች ሥራቸውን ለማሳደግ የሚገጥማቸውን ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ተጠቆመ
November 6, 2025
እንተርፕራይዞች ሥራቸውን ለማሳደግ የሚገጥማቸውን ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ተጠቆመ
በተለያየ ደረጃ የሚገኙ እንተርፕራይዞች ሥራቸውን ለማሳደግ የሚገጥማቸውን ችግር ለመቅረፍ ያለመ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የሥልጠናና የተቋማት አቅም ግንባታ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙህዲን አባ ሞጋ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና አጠናቃቂዎችና ኢንተርፕራይዞች ከሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች መካከል አንዱ የሥራ መጀመሪያና ማስፋፊያ ካፒታል እጥረት ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍም መንግስት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዚህም የጥቃቅን አነስተኛ እና መካከለኛ እንተርፕራይዞች ቢዝነሳቸውን ለማሳደግ የሚያግዛቸውን የአቅም ግንባታ ሰልጠና የብድር አቅርቦት ላይ የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡
የብድር አቅርቦት ጋር ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከስድስት ባንኮች ጋር ያለማስያዣ ወጣት ሥራ ፈጠሪዎች ብድር የሚያገኙበት መንገድ ተመቻችቶ ወደ ሥራ መገባቱ እና በቅርቡም የወጣጦች የሥራ ፈጠራ ኢንቨስትመንት ባንክ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱንም አስረድተዋል፡፡
ብድር የማግኘት ሂደቱ ከባንኮች መደበኛ የአሠራር ሂደት የተለየና ቀላል መሆን እንዳለበት፤ የንግድ ክህሎት ስልጠና የገንዘብ አያያዝና ብድር እንዲሁም የአቅም ግንባታ ሰልጠና መሰጠት እንዳለበት የመድረኩ ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡
ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በአነስተኛ ንግድ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች ከባንኮች በቀላሉ ብድር አግኝተው ሥራቸውን በማስፋፋት የኢንተርፕራይዞችን የመሞት ምጣኔ ለማሰቀረት እየተሰራ መሆኑም በዕለቱ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ ላይ ከአስራ አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ ክፍለ ከተማዎችና እና ከ12ቱ ሸገር ከተማ አስተዳዳር የሥራ ማዕከላት አስተባባሪዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ዲንና ምክትል ዲኖች ተገኝተዋል፡፡





