Mols.gov.et

ኢንስቲትዩቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ ከ10 በላይ አዳዲስ የስልጠና ፕሮግራሞች መጀመሩ አስታወቀ፡፡

October 9, 2025
ኢንስቲትዩቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ ከ10 በላይ አዳዲስ የስልጠና ፕሮግራሞች መጀመሩ አስታወቀ፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተጠሪ የሆነው የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዜጎች ስለተቋሙ አገልግሎት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ የሚያስችል የመረጃ ሳምንት በይፋ አስጀምሯል፡፡ የመረጃ ሳምንቱን አስመልክተው ለሚዲያ አካላት ማብራሪያ የሰጡት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር(ዶ/ር) የመረጃ ሳምንቱ ዜጎች ተቋሙ ስለሚሰጣቸው አገልግሎቶች እና ስለሚሰጣቸው ስልጠናዎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ታስቦ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ በሀገራችን የብቃት ማዕቀፍ ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 8 የፒኤች ዲ ደረጃ ድረስ ስልጠና መስጠት የሚችል ብቸኛ ተቋም መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በዘንድሮ አመት ብቻ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ ከ10 በላይ አዳዲስ የስልጠና ፕሮግራሞች መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ የመቁረጫ ነጥብ በላይ ያመጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ በደረጃ 6 ዲግሪ፣ በደረጃ ሰባት ማስተርስ እና ደረጃ ስምንት ፒኤችዲ ማስልጠን እንደሚጀምር አብራርተዋል፡፡ በደረጃ 6 በቅድመ ምረቃ የሚጀመሩት ባዮሜዲካል ቴክኖሎጂ፣ ሳይበር ሰኩዩሪቲ ቴክኖሎጂ ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ኒው ኢነርጂ ቬሂክል ቴክኖሎጂ ፣ ፕላስቲክ ቴክኖሎጂ፣ ሆርቲካልቸር እና ኢንተለጀንት ሮቦቲክስ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ በደረጃ 7 በድህረ ምረቃ ፕሮግራም ደግሞ ኢንቴርየር ዲዛይን እና ሌዘር ፕሮዳክት ቴክኖሎጂ እንዲሁም በደረጃ 8 በፒኤች ዲ ደረጃ በቲቬት ሊደርሺፕ እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ስልጠና ይሰጣል ብለዋል፡፡ ተቋሙ ብቁ ሰልጣኞች ያሉት እና የተሟላ ግብዓት ያለው በመሆኑ ዜጎች በእነዚህና በሌሎችም በፈለጉት የሙያ ዘርፍ ገብተው ሰልጥነው ዘመን የማይሽረውን ክህሎት እንዲታጠቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top