ኢንስቲትዩቱ ሰዎችንና ተቋማትን የሚቀይር ሥራ የሚሰራ ትልቅ የሀገር ሀብት ነው
December 16, 2025
ኢንስቲትዩቱ ሰዎችንና ተቋማትን የሚቀይር ሥራ የሚሰራ ትልቅ የሀገር ሀብት ነው
የተከበሩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እያደረገ የሚገነውን የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ቀጥሎ በኢንተርሪነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡
የኢንስቲትዩቱ አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ፣ የተገኙ ውጤቶች እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ገለፃ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፣ የመስክ ምልከታው ዓላማ የኢንስቲትዩቱን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክቶ ተግዳሮቶችን መፍታት እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
ከቢሮ አደረጃጀት ጀምሮ ኢንስቲትዩቱ በብዙ ቦታዎች ያልተለመደና ለሥራ ምቹ የሆነ ከባቢ መፍጠር መቻሉን አንስተው፤ አፈፃፀሙም ትልቅ ነገርን አስቦ በማቀድ፤ አቅዶም በመተግባር የሚመጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ሰዎችንና ተቋማትን የሚቀይር ሥራ የሚሰራ ትልቅ የሀገር ሀብት እንደሆነም የተከበሩ ዶ/ር ገልፀዋል፡፡
ተግዳሮቶችን ወደ ዕድል በመቀየርና ፀጋዎቻችንን በአግባቡ በማልማት እንደ ሀገር ወደፊት እንዳንሄድ ያደረጉንን እንቅፋቶች ሁሉ እንድናልፍና ወደ ግባችን እንድንደርስ የሚያደርግ በመሆኑ አቅሙን ማባዛትና ሥራውን ማስፋት እንደሚገባውም ጠቁመዋል፡፡
ሀገርና ተቋም የሚቀየረው ትክክለኛ አመራር ሲኖር ነው ያሉት የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ፤ ሰርተው የሚያሰራና የማያሰሩ ቢሮክራሲዎችን የሚገሩ አመራሮችን ለማፍራት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ቤተልሔም ላቀው በበኩላቸው፤ በተቋሙ ሪፖርት ችግር አለመቅረቡን ገልጸው ይህም ችግሮችን ወደ መልክም እድልነት የሚቀይር ተቋም መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ባልተለመደ መንገድ በመሄድ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልፀው ውጤቱን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋት በተቋማት አመራሮች ላይ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመላክተዋል፡፡
የኢንተርፕሪነርሺፕ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር ሀሰን በበኩላቸው፣ ኢንስቲትዩቱ የኢንተርፕሪነርሺፕ ስነ-ምህዳሩን በማስፋት ሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር የተቋማት አመራሮችን አቅም ከማሳደግ አኳያ እያደረገ ያለውን ጥረትና የተገኙ ውጤቶችን አብራርተዋል፡፡
በኢንተርፕሪነርሺፕ ስነ-ምህዳር ግንባታ ኢትዮጵያ ምንም ከማትታወቅበት ምራፍ ወጥታ በዚህ ዓመት በዓለም አቀፍ መድረክ የመጀመሪያ ደረጃ መያዟንም ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይ የዓለማችን ታላለቅ ባለሀበቶችና ኢንቨስተሮች የሚሳተፉበትን የኢንተርፕሪነርሺፕ ኮንግረንስ ለማዘጋጀት ጥያቄ መቅረቡንም አንስተው ለስነ-ምህዳር ግንባታው ቋሚ ኮሚቴው ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡













