Mols.gov.et

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የብየዳ ኢንስቲትዩት (IIW) …

July 25, 2026
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የብየዳ ኢንስቲትዩት (IIW) የ2026 ይፋዊ የአባልነት ሰርተፊኬት ተረከበች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የብየዳ ኢንስቲትዩት (International Institute of Welding–IIW) 79ኛ ዓመታዊ ጉባኤ በቦርድ አባላት በሙሉ ድምፅ ከጸደቀች በኋላ፣ የ2026 ይፋዊ የአባልነት ሰርተፊኬቷን በይፋ ተረክባለች። ኢትዮጵያን በዚህ ዓለም አቀፍ ተቋም የሚወክለው የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የብየዳ ልህቀት ማዕከል ነው። ይህ አባልነት ኢትዮጵያ በብየዳ ቴክኖሎጂ፣ በክህሎት ልማት እና በዓለም አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ትብብር ውስጥ እያሳየች ያለችውን እድገት የሚያረጋግጥ ታላቅ ዓለም አቀፍ እውቅና ነው። የIIW የአስተዳደር፣ ኮሙኒኬሽን እና ሁነቶች ኃላፊ ሮሳሪያ ሩሶ (Rosario Russo) በላኩት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት፣ ኢትዮጵያን ወደ IIW ቤተሰብ በመቀላቀሏ ያላቸውን ደስታ ገልጸው፣ ይህ አባልነት የዕውቀት ልውውጥን ለማጠናከር፣ የሙያ ብቃትን ለማሳደግ፣ ዓለም አቀፍ የሙያ ትስስርን ለማስፋት እና የጋራ ምርምርና ፈጠራን ለማበረታታት አስፈላጊ መሠረት እንደሚሆን ማስታወቃቸውን ከኢኒስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ለኢትዮጵያ ይህ ስኬት ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የብየዳ ስልጠና፣ የብቃት ማረጋገጫ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማጠናከር አዲስ እድል የሚፈጥር ሲሆን፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለኮንስትራክሽን፣ ለማኑፋክቸሪንግ እና ለሌሎች የምርት ዘርፎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የብየዳ ልህቀት ማዕከል በዘርፉ በሀገር ደረጃ ብቸኛ የልህቀት ማዕከል ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች በማፍራት የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
en_USEN
Scroll to Top