Mols.gov.et

በ270 ቀበሌዎች 32000 ወጣት ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል…

June 23, 2026
በ270 ቀበሌዎች 32000 ወጣት ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የጋራ ስምምነት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በክህሎት ልማትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ረገድ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነት ‹ ፖፑሌሽን ሰርቪስ ኢንተርናሽናል› (PSI/E) ከተሰኘ ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋማ ጋር ተፈራረመ፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ተሻለ በሬቻ( ዶ/ር ) በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚያስፈፅማቸው ተልዕኮዎች የባለድርሻ አካላትን ርብርብ በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈልጉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በዚሁ መሠረት‹‹ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከበርካታ ተቋማት ጋር የመግባባያ ሰነድ በመፈራረም ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በአጋርነት እያከናወነ ይገኛል›› ብለዋል፡፡ ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ “ደረጃውን ወደጠበቀና ወደ ምሉዕ የሥራ እድል ማደግ” (Step Up to Dignified and Fulfilling Work) በሚል ስያሜ ለሦስት ዓመታት የሚተገበረው ይህ ፕሮግራም በአጠቃላይ 32 ሺህ ወጣት ሴቶችን ተደራሽ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ፕሮግራም ስር 32 ሺህ ለሚሆኑት ወጣት ሴቶች የፋይናንስ አቅማቸውን የማጠናከር ሥራ የሚሠራላቸው ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 24 ሺህ ለሚሆኑት ወጣት ሴቶች ደግሞ የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ ይሰራል፣ በተጨማሪም ከ4 ሺህ በላይ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች እንደሚፈጠሩ በዕቅዱ ተካቷል፡፡ ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በፌዴራል የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና በፖፑሌሽን ሰርቪሰስ ኢንተርናሽናል (PSI) መካከል በጋራ ዲዛይን በማድረግ (co-creation) የተጀመረ ሲሆን፤ ዋና ዓላማውም ዕድሜያቸው ከ15-35 ለሆኑ ወጣት ሴቶች የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ፣ የትምህርት፣ የክህሎት እንዲሁም የሥራ ዕድሎችን በማስፋት የድህነት ቅነሳን ማፋጠን ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በተለይም የመሰረተ ልማት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ወጣቶችን የአካታች እድገትን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፣ የማህበረሰብን ችግሮች ለመፍታት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ይህ የረጅም ጊዜ አጋርነት የፕሮጀክቱ ዘመን ከመጠናቀቁ በፊት ለታለሙ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘላቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድልን የማስገኘት ስትራቴጂካዊ ግብን እንደሚያሳካ ታምኖበታል፡፡
en_USEN
Scroll to Top