Mols.gov.et

በግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች መመሪያ ማሻሻያ እና በዲጂታል አሠራር ትግበራ ላይ …

June 15, 2026
በግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች መመሪያ ማሻሻያ እና በዲጂታል አሠራር ትግበራ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከጀርመን የልማት ድርጅት(GIZ) ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ‹‹በሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪት መመሪያ ማሻሻያ እና በዲጂታል አሠራር ትግበራ›› ዙሪያ የሚያተኩር አገር አቀፍ የውይይት መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ከግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎችና ጉዳዩ የሚመለከታው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተሳታፊ የሆኑበትን ይህን መድረክ በንግግር የከፈቱት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመንና ተደራሽነቱን ለማስፋት መድረኩ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዜጎችን የዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሪፎርም ሥራዎችን በቁርጠኝነት እያከናወነ እንደሚገኝ የተናገሩት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ዜጎች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ተገቢውንና ክብር ያለው የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ከነዚህ ስትራቴጂካዊ ሪፎርሞች መካከል ግንባር ቀደሙ የሥራ ገበያውን ዘመናዊና ተደራሽ ማድረግ ሲሆን፤ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የኢትዮጵያ ሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት (E-LMIS) የመበልጸግ ሥራ ተጠናቆ፣ ሥራና ሠራተኛ በዲጂታል ፕላትፎርም በቀላሉ የሚገናኙበት የቴክኖሎጂ ሥርዓት ተዘርግቶ ወደ ሥራ መግባቱ ተገልጿል፡፡ መንግሥት በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪት አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታ ለመወሰን መመሪያ ቁጥር 45/2013 አዘጋጅቶ ባለፉት አምስት ዓመታት ሥራ ላይ የዋለ ቢሆንም አተገባበር ላይ በተደረጉ ዳሰሳ ጥናቶች የአፈጻጸም ክፍተቶችና ውስንነቶች መስተዋላቸውን ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ ገልፀዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ አጋጣሚዎች በሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎችና የመብት ጥሰቶች መኖራቸውን መረጃዎች እንደሚያመላክቱ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የመብት ጥሰት በበቂ መረጃ ላይ ተመስርቶ ሲቀርብ፣ መንግሥት አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ ያለማወላወል እንደሚወሰድ ሁሉም ወገን ሊገነዘበው ይገባል” ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የተሸሻለው መመሪያ ሠራተኛውን፣ አሠሪውንና ኤጀንሲዎችን በእኩልነትና በፍትሐዊነት ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችል የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለተግባራዊነቱ ርብርብ እንዲያደርጉ በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top