Mols.gov.et

በድሬደዋ የወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚነት…

May 13, 2026
በድሬደዋ የወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚነት ያሳደጉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ -ከንቲባ ከድር ጁሃር በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ። የሀገር ውስጥና የውጭ አገራት የስራ ስምሪትን ለማመቻቸት ያለመ የአሰሪና ሰራተኞች አገናኝ ዐውደ ርዕይ ዛሬ በድሬደዋ ተካሂዷል። የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንዳሉት በድሬደዋ የወጣቶችን የስራ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎትና በሌሎችም ዘርፎች አማራጮችን በማስፋት ላይ ይገኛል። ተግባሩን ለማስቀጠልም ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠኑ 350 ወጣቶች በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የስራ እድል እንዲያገኙ መደረጋቸውን ገልጸው፤ ለዚህም የዛሬው መርሃ ግብር መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። በተጨማሪም በሀገር ውስጥ የስራ ስምሪት ለሚሳተፉ ወጣቶችም በአሰሪና ሰራተኞች አገናኝ ድርጅቶች አማካኝነት 380 ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል መመቻቸቱን ገልጸዋል። የድሬደዋ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው በበኩላቸው ወጣቶች በዕውቀትና በክህሎት ተወዳዳሪ በመሆን የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ሴክተር መስሪያቤቶች እና ባለሃብቱ በቅንጅት እንዲሰሩ የተለያዩ መድረኮች መካሄዳቸውን ጠቁመው የአሁኑ ዐውደ ርዕይም የቅንጅታዊ ስራው ማሳያ ነው ብለዋል። ከሀገር ውስጥ የስራ ስምሪት ባለፈ ወደ ውጭ ሀገራት ለሚጓዙት ወጣቶች የቋንቋ፣ የአካባቢዎቹ መረጃዎችና ሙያዊ ስነምግባር ላይ ተገቢውን ስልጠና በመውሰድ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ መሰራቱን አንስተዋል። ዘገባው ኢዜአ ነው።
en_USEN
Scroll to Top