Mols.gov.et

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት …

July 28, 2026
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ቅንጅታዊ አሠራሮችን ለማጠናከር ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ተገለጸ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መርህ መሠረት በማጠናከር፣ የዜጎችን መብት፣ ደህንነትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ በሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ባካሄዱት የጋራ ውይይት ተገልጿል። በውይይቱ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል፣ ክቡር አምባሳደር ደዋኖ ከድር፣ ክቡር አምባሳደር አዲስዓለም መለሰ እንዲሁም የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል። ውይይቱ በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ዘርፍ እስካሁን የተመዘገቡ ውጤቶችን፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን እና የቀጣይ የጋራ ትኩረት አቅጣጫዎችን በስፋት ገምግሟል። በተለይም የሁለቱ ሚኒስቴሮች የተቀናጀ አሠራር ሕጋዊ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን ይበልጥ ምቹ፣ ቀልጣፋ፣ ግልጽና ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል። በዚህ መሠረት የመረጃ ልውውጥን፣ የተቀናጀ ክትትልን፣ የጋራ የተግባር አፈጻጸምን እና የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራርን ይበልጥ በማጠናከር የሕጋዊ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አገልግሎቶችን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ፣ የዜጎችን መብት፣ ደህንነትና ክብር በተሻለ ሁኔታ ለማስጠበቅ እንዲሁም የዜጎችንና የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም የሚያሳድጉ ተግባራት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ተመላክቷል። በውይይቱ ላይ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መርህ መሠረት በሀገር ውጭ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን መብትና ደህንነት እንዲጠበቅ፣ ሕጋዊ የሥራ ስምሪት ሥርዓቱ የተቀናጀ፣ ግልጽ እና ተጠያቂነት ያለበት እንዲሆን ሁለቱ ተቋማት ያላቸውን ትብብር የበለጠ እንደሚያጠናክሩም ተገልጿል። ይህ ቅንጅታዊ አሠራር ሕጋዊ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን የበለጠ ውጤታማ ከማድረጉ ባሻገር፣ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ተጠቁሟል።
en_USEN
Scroll to Top