በውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት ላይ የተኮረ ውይይት ተካሄደ
July 27, 2026
በውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት ላይ የተኮረ ውይይት ተካሄደ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀምና በ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የምክክር መድረክ ከውጭ ሀገር አሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጋር አካሄደ፡፡
በውይይቱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የአሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ፤ በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት አዋጅን ወደ ሥራ ማስገባት ዋንኛው እንደሆነ በመጠቆም አዋጁን ለማስፈፀም የሚያስችል መመሪያም በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የስልጠናና የምዘና ተቋማት አገልግሎትን ጨምሮ የመዳረሻ ሀገራት አሰራሮችን ማሻሻል፣ ለአቅም ግንባታ የሚረዱ ስልጠናዎችን መስጠትና ከኤጀንሲዎች ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ የምክክር መድረኮችን ማካሄድ በልዩ ትኩረት ከተከናወኑ ተግባራት መካከል እንደሚጠቀሱ ተብራርቷል፡፡
በነበሩት የተቀናጁ ጥረቶች በበጀት ዓመቱ ከ630 ሺህ በላይ ዜጎችን ከውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ በመድረኩ ተመላክቷል፡፡
በቀጣዩ የ2019 በጀት ዓመትም የሰለጠነና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል በስፋት የመላክ ዕቅድ መያዙን የገለፁት ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ ህገወጥ አሰራሮችን ለማስወገድ በትኩረት እንደሚሰራም በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
ተገቢውን የገበያ ጥናት በማካሄድ የመዳረሻ ሀገራትን ማስፋት፣የአሰራር ችግሮችን በጥናት በመለየት ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጡ ሥርዓቶችን መዘርጋት ዘርፉ ምቹና ውጤታማ ሥነ ምህዳር እንዲኖረው ለማስቻል የተቀመጡ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የውጭ ሀገር ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የዜጎችንና የሀገርን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያላቸውን ጉልህ ድርሻ ተገንዝበው ሥራውን በኃላፊነትና በታማኝነት መፈፀም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
አክለውም በኤጀንሲዎች መካከል የሚስተዋሉ ችግሮችን በውይይት መፍታት፣ ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር ህገወጥ አሰራሮችን በጋራ መታገል እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡











