በክህሎትና በሙያ የበቁ ዜጎችን ለማፍራት የአሰልጣኝ መምህራን የክህሎት ብቃት ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ ።
October 9, 2025

በክህሎትና በሙያ የበቁ ዜጎችን ለማፍራት የአሰልጣኝ መምህራን የክህሎት ብቃት ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአዲሱ እሳቤ የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ የሥልጠና ጥራትን ማስጠበቅ ነው፡፡
ይህንንም መሰረት በማድረግ ቀደም ብሎ ለክልል ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ለተውጣጡ አሰልጣኝ መምህራን ስልጠና መስጠቱ ይታወሳል፡፡
የሲዳማ ክልል የሥራና ክህሎት ቢሮም በበኩሉ ለቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አሰልጣኝ መምህራን ለ20 ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የቆየውን የክህሎት ክፍተት ማሟያ ስልጠና መጠናቀቁን አሳውቋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል የሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ሀላፊና የሙያ ስልጠናና የኢንተርፕራይዞች ድጋፍ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ፍስሃ ፍቾላ በዕውቀትና በክህሎት የበቃ የሰው ሀይል ማፍራትና በተለዋዋጭ አለም የሚመጥን ዜጋን ማፍራት የዘርፉ ተልዕኮ መሆኑን ገልፀዋል ።
ለ20 ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የቆየው የአሰልጣኞች የክህሎት ማሟያ ስልጠና በስስ ክህሎት እና በተግባር ተኮር ስልጠና ዘርፎች ለሁለት ተከፍሎ መሰጠቱን ጠቅሰው ስልጠናውም የሪፎርም ትግበራ ለማጠናከር እንደሚረዳ አያይዘው ተናግረዋል።
ከኢንዱስትሪዎች ጋር በመቀናጀት በተሰራው ሥራ የስልጠና ጥራት ለማረጋገጥና የግብዓት ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ እገዛ እንዳደረገም ገልጸዋል ።
የሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ወርክ ሾፖችንና የሰው ሀይል በማዘጋጀት ለሥልጠናው ስኬት ትልቅ ድርሻ መወጣቱን አንስተው በዚህም ያስቀመጥነው ግብ ማሳካት ችለናል ብለዋል።
በመቀጠል በክላስተር ደረጃ የሚሰጥ ስልጠና ጥቅምት 10/2018 ጀምሮ በተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
በስልጠናው 340 የሚሆኑ አሰልጣኝ መምህራን መሳተፋቸው የተገለፀ ሲሆን ስልጠናውን በብቃት ሲያሰለጥኑና ሲሰለጥኑ ለቆዩ አሰልጣኞችና ሰልጣኝ መምህራን የዕውቅናና የምስጋና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።
መስከረም 29/2018 ዓ.ም ፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር





