በአፍሪካ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የሴቶችና የወጣቶችን ተሳታፊነት ዕውን ማድረግ ቀዳሚው አጀንዳ ሊሆን ይገባል፡፡ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ
December 19, 2024
በአፍሪካ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የሴቶችና የወጣቶችን ተሳታፊነት ዕውን ማድረግ ቀዳሚው አጀንዳ ሊሆን ይገባል፡፡
ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ
የሴቶችና የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ‹‹የአፍሪካ የሥራ ፈጠራ ፎረም›› በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
ፎረሙ አፍሪካውያን ሴቶችና ወጣቶች በፍጥነት እያደገ ከሚገኘው ዲጂታል ኢኮኖሚ በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሚያስችሉ አጀንዳዎች ያተኮረ ነው፡፡
በፎረሙ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ አፍሪካ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋና ሰፊ የወጣት ቁጥር ተጠቅማ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የሴቶችና የወጣቶችን ተሳታፊነት ዕውን ማድረግ ቀዳሚው አጀንዳ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ወጣቶችን የዲጂታል ቢዝነስና የፋይናነስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የኢትዮጵያ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ የገለፁት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በቀጣይም ከግል ዘርፎችና ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር የኢትዮጵያውያን ኢንተርፕሪነሮችን ስኬታማነት የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ለመከወን የሚያስችሉ ዕቅዶች መነደፋቸውን አብራተዋል፡፡
በተለያየ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በማሳደግና በማስፋት ረገድም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አበረታች የሆኑ ተሞክሮዎችን እያስመዘገበ እንደሚገኝ ክቡር አቶ ሰለሞን ጠቁመዋል፡፡
የሴቶችና ወጣቶች የፋይናነስ ተጠቃሚነት 2030 ሙሉ ለሙሉ እውን ለማድረግ የተያዘው ዕቅድም( WYFIE 2030) ሆነ አፍሪካውያን በጋራ የሚገበያዩበት ዲጂታል ፕላትፎርም (Sokokuu-Africa) ለማልማት እየተደረገ ካለው ጥረት ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም በመድረኩ ተመላክቷል፡፡
የአፍሪካውያን ሴቶችና ወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ከሚያደርገው ውይይት ጎን ለጎን ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሳተፉበት ኤግዚቢሽንና ባዛር ተካሂዷል፡፡