Mols.gov.et

በታዳሽ ኃይል ዙሪያ የሥልጠና ፕሮግራሞችን መክፈትና አዋጪነት

November 21, 2025
በታዳሽ ኃይል ዙሪያ የሥልጠና ፕሮግራሞችን መክፈትና አዋጪነት የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት የታዳሽ ሃይል ቴክኖሎጂን ለመጠቀም የሚያስችል የሥልጠና ፕሮግራም ለመክፈት የእሴት ሰንሰለት ትንተናን መሰረት አድርጎ በተሠራ የዳሰሳ ጥናት ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡ በጥናቱም ታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ የሚገኝባቸው አምስት ተፈጥሯዊ ሃብቶችን በተመለከተ ዘርዘር ያለ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ወንዞቿን በመጠቀም 45ሺ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ከ5-6 ኪሎዋት ፐር ሀወር ስኩዌር ሜትር የፀሀይ ሃይል፣ 10ሺ ሜጋ ዋት የንፋስ ሀይል፣ 10ሺ ከጂኦተርማል እና ከ2.8-8.8 ሚሊዮን ቶን በአመት ቆሻሻን ወደ ሀይል በመቀየር ማምረት የምትችል ቢሆንም እስካሁን ጥቅም ላይ የዋለው እጅግ ውሱን መሆኑ ተነስቷል፡፡ በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር፣ የመሰረተ ልማት እጥረት እና የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ታዳሽ ኃይልን በበቂ መጠን ጥቅም ላይ ላለመዋሉ ዋንኛ ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎች ‹‹የአለም አቀፍ የነዳጅ ገበያዎች ላይ ጥገኛ መሆንን ትተን በተለይ በአሁኑ ሰአት ኤሌክትሪክ መኪኖችን መጠቀም መጀመራችን ተለዋጭ ኃይሎችን እንድንጠቀም ያስገድደናል በተጨማሪም ታዳሽ ኃይሎች ዘላቂ እና በአጠቃቀም የማይሟጠጡ ስለሆኑ እና ለኢኮኖሚው እድገትም ወሳኝ ሚና ስላላቸው ተመራጭ ናቸው›› የሚል ሃሳብ በስፋት አንስተዋል፡፡ በመሆኑም በሀገራችን የሚገኙ የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በማጥናት በአጭር እና በረጅም ጊዜ የሥልጠና ፕሮግራሞችን መክፈት አስፈላጊ መሆኑ በአፅንኦት ተነስቷል፡፡
en_USEN
Scroll to Top